የእስራኤል ተቃዋሚዎች አዲስ የአንድነት መንግሥት ለማቋቋም ተስማሙ

ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – የእስራኤል ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቤንጃሚን ኔታንያሁን የ12 ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚያከትም አዲስ መንግሥት ለማቋቋም ከስምምነት ደረሱ፡፡

የየሽ አቲድ ፓርቲ መሪው ያይር ላፒድ በስምንት ቡድኖች የተቋቋመ ጥምረት መመስረቱን አስታውቀዋል፡፡

ሥልጣን በዙር በሚከፋፈልበት በዚሁ ስምምነት መሠረት የያሚና ፓርቲው አለቃ ናፍታሊ ቤኔት በቀዳሚነት ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑ ሲሆን፣ በቀጣይ ላፒድ ሥልጣኑን ይረከቧቸዋል ነው የተባለው።

መንግሥት ለመመስረት ቃለ መሐላ ከመፈጸሙ በፊት የፓርላማው ይሁንታ ያስፈልጋቸዋልም ተብሏል፡፡

ላፒድ በሰጡት መግለጫ ስለስምምነቱ ለፕሬዝዳንት ሬውቨን ሪቭሊን ማሳወቃቸውን ገልጸው፣ “ይህ መንግስት ሁሉንም የእስራኤል ዜጎች፣ የመረጡትንም ሆነ ያልመረጡትን ለማገልገል እንደሚሠራ ቃል እገባለሁ” ብለዋል፡፡

“ተቃዋሚዎቻቸውን የሚያከብር ሲሆን፣ ሁሉንም የእስራኤልን የህብረተሰብ ክፍሎች አንድ ለማድረግ እና ለማገናኘት የቻለውን ሁሉ ያደርጋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በእስራኤል የመገናኛ ብዙሃን በተሰራጨ ምስል ላፒድ፣ ቤኔት እና የአረብ ኢስላሚስት ራም ፓርቲ ሊቀመንበር ማንሱር አባስ ስምምነቱን ሲፈርሙ ቢታዩም ብዙዎች የማይቻል መስሏቸው ነበር፡፡

አባስ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት “ውሳኔው ከባድ እና በርካታ ክርክሮች ነበሩት። ስምምነቶቹ ላይ መድረስ ግን አስፈላጊ ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት ለአረብ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚጠቅም ብዙ ነገሮች አሉት” ብለዋል፡፡

ላፒድ ለፕሬዝዳንቱ በላኩት ማስታወሻ እ.አ.አ ነሐሴ 27/2023 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እስከሚሾሙ ድረስ ከቤኔት ጋር በመሆን መንግስትን እመራለሁ ብለዋል፡፡

ሪቭሊን በጉዳዩ ላይ የመተማመኛ ድምጽን በተመለከተ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ፓርላማው በተቻለ ፍጥነት እንዲሰበሰብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህብረቱ በ120 መቀመጫዎች ባሉት ክኔሴት (የእስራኤል ፓርላማ) የአብላጫውን ድጋፍ ማግኘት ካልቻለ ሃገሪቱ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ ትገደዳለች፡፡

ጥምረት የፈጠሩት ፓርቲዎች የእስራኤልን ፖለቲካ ሙሉ ገጽታ ያሳያሉ ተብሏል፡፡ ፓርቲዎቹ ኔታንያሁን ለመተካት ከማቀድ ውጭ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ብዙም የሚያመሳስላቸው ነገር የለም ነው የተባለው፡፡

የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ ከወራት በፊት በተደረገው ምርጫ ብዙ ወንበር ቢያገኝም ስልጣን የሚያስገኝለትን ጥምረት መመስረት አልቻለም።

ኔታንያሁ የታቀደው አዲስ መንግስት “የክፍለ ዘመኑ ማጭበርበር” ሲሉ ገልጸው የእስራኤልን መንግሥት እና ህዝቡን አደጋ ላይ የሚጥል ብለውታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡