የካራማራ ጦርነት 43ኛ ዓመት የድል በዓል እየተከበረ ነው

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – የካራማራ ጦርነት 43ኛ ዓመት የድል በዓል በአዲስ አበባ በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ነው።

በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሥራ ኃላፊዎች፣ በካራማራ ጦርነት የተሳተፉ የወቅቱ የሠራዊት አባላት እና ልጆቻቸው እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በየነን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያስተዳደሩት ሲያድ ባሬ “ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል” በማለት በ1969 ግልጽ ወረራ ኢትዮጵያ ላይ ፈጸሙ።

የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኩባ ወታደሮችም የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ጦር የዚያድ ባሬን ጦር ካራ ማራ ላይ ድል በማድረጉ የኢትዮጵያ አሸናፊነት በአደባባይ ታወጀ።

ከኢትዮጵያዊያን የየካቲት ወራት ድሎች አንዱ የሆነው የካራማራ ድል 43ኛ ዓመቱን አስቆጥሮ የድል በዓሉ በኢትዮጵያዊያን እየተከበረ ነው።

በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ባለው የድል በዓል የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በጦርነቱ ለተሰው ጀግኖች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።