የኬንያ አየር መንገድ በታሪኩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ደረሰበት

የኬንያ አየር መንገድ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – ግዙፍ ከሚባሉት የአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው የኬንያ አየር መንገድ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን ኪሳራ እንዳጋጠመው ተገለጸ።

ለበርካታ ዓመታት በኪሳራ ውስጥ ሆኖ የአገሩን ስም ሲያስጠራ የቆየው አየር መንገዱ፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከፍተኛ የተባለለትን 332 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ ተመዝግቦበታል።

የኬንያ አየር መንገድ ቀደም ባለው ዓመትም የ118 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ የገጠመው ሲሆን፣ የአሁኑ ግን እጅግ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

ያጋጠመው ኪሳራ ከ2019 የፈረንጆቹ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ179 በመቶ ሲያሻቅብ፣ ለኪሳራ በምክንያትነት የተጠቀሰው በኮቪድ-19 ምክንያት ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲቆሙ መደረጋቸው ነው ተብሏል።

የኬንያ አየር መንገድ እንዳለው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተጓዦች ቁጥር ወትሮ ከነበረው በ65.7 በመቶ ሲቀንስ ይህም የ473 ሚሊየን ዶላር ገቢ አሳጥቶታል።

የኬንያ አየር መንገድ ሊቀመንበር ማይክል ጆሴፍ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ማንም የገመተው አልነበረም፤ በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖም ለመጪዎቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል” ሲሉ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ካጋጠመው ኪሳራ ለመውጣት ሲጥር ለነበረው አየር መንገድ ያለፈው ዓመት ኪሳራ ከባድ ጉዳትን አስከትሎበታል ተብሏል።

ሊቀመንበሩ ጨምረውም የአየር መንገዱ የወደፊቱ ሁኔታ አሁንም ተስፋ ሰጪ እንዳልሆነ እና ከገጠማቸውን ከባድ ፈተና ለመውጣት የሚያስችል አማራጭ በመፈለግ ጥረት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ አየር መንገዱ ኪሳራውን ለመቀነስ ሲል ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 650 ሠራተኞቹን የቀነሰ ሲሆን፣ በተቀሩት ሠራተኞቹ ላይ ደግሞ የደሞዝ ቅነሳ አድርጓል።

በተጨማሪም የተወሰኑ ንብረቶቹን እንደሸጠና ለመንገደኞች አገልግሎት ይውሉ የነበሩ አንዳንድ አውሮፕላኖቹን ደግሞ ወደ ጭነት ማጓጓዣነት መቀየሩ ተገልጿል።

ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር እንደተነበየው በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተከሰተው የአየር ትራንስፖርት መስተጓጎል ምክንያት የአፍሪካ አየር መንገዶች አስከ 6 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ሊገጥማቸው ይችላል።

በዚህም ሳቢያ በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ 172 ሺህ ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል ችግር ይገጥማቸዋል ማለቱን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል፡፡