የክልል ርእሰ መስተዳድሮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

የክልል ርእሰ መስተዳድሮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልእክት፣ ዘመናትን ያስቆጠረው የሕዝቦች በሰላም በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴት ማጠናከር ከሁሉም የክልሉ ነዋሪ የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማብላት እና የተጠሙትን በማጠጣት የተለመደ የመተዛዘን እና የመረዳዳት ባሕልን በተገበረ መልኩ መሆን አለበት ብሏል፡፡

ኅብረተሰቡ ኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንጻር እያሳየ ያለውን የመዘናጋት ችግር በመቅረፍ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲከላከል የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት፣ የክርስቶስን ልደት ተከትሎ አዲስ ተስፋ እና ሕይወትን እንደለገሰን ሁሉ እኛም በአዲስ መንፈስ እና አስተሳሰብ የጀመርነው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በተሰማራንበት መስክ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡም ለኮቪድ-19 ያለው ዝቅተኛ ግምት እያደር ዋጋ ሊያስከፍለን ስለሚችል አስፈላጊ ሁሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ኅብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር በመረዳዳትና በመተሳሰብ በአብሮነት ሊሆን እንደሚገባ፣ እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ራሱን እየጠበቀ እና የመከላከያ እርምጃዎች እየወሰደ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

“የአገራችን ሕዝቦች ብዝኃነታችሁን እንደ ውበት ወስዳችሁ፣ ኢትዮጵያን  በጋራ ለመገንባት ወስናችሁ፣ የብልጽግና ብርሃን ከፊት እያያችሁ የጀመራችሁትን ረጅም ጉዞ በስኬት እንደምታጠናቅቁ ጥርጥር የለኝም” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡

የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግሥት ባስተላለፈው መልእክት እንዲሁ ኅብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር በመተከል ዞን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን በመደገፍ መሆን እንዳለበት ገልጿል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በማክበር ሂደት በሚያደርጉት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የኅብረተሰቡ የጤና ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 መከላከያ እና የጥንቃቄ መንገዶችን በልዩ ትኩረት በመተግበር ራሳቸውን ከቫይረሱ ሊጠብቁ እንደሚገባም የክልሉ መንግሥት ጥሪ  አቅርቧል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፣ በዓሉን ስናከብር ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን፣ አቅመ ደካሞችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዓመት የገና በዓል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጠላት በሆነው ኃይል ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ በተወሰደበት ማግስት በአዲስ መንፈስ በልዩ ሁኔታ የሚከበር መሆኑንም ተናግረዋል።