የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሁሉም ቦታ የተቀመጡ ህጎችን እና ጥንቃቄዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – እየጨመረ  የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል በሁሉም ቦታ የተቀመጡ ህጎችን እና ጥንቃቄዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሁሉም ቦታ የተቀመጡ ህጎችን እና ጥንቃቄዎችን ማጠናከር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ባለፈው አመት መልካም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ስራ የሰራችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተስተዋሉ ባለው ቸልተኝነትና መዘናጋት የወረርሽኙ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረ በተደጋጋሚ እየተገለፀ ነው።

ከስርጭቱ መስፋፋትና መጨመር ጋር ተያይዞ የፅኑ ህክምና ታማሚዎችና በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እጅግ አሻቅቧል።

ለወረርሽኙ መጨመር የህበረተሰቡ የማስክ አጠቃቀም እና የጥንቃቄ ጉድለቶች በዋናነት የተጠቀሱ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ውስን የመመርመር አቅም ያላት ሲሆን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞም የፅኑ ህሙማን ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ከወረርሽኙ ክትባት ጋር በተያያዘም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ እድሚያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑና እንዲሁም ተያያዥ ህመም ያለባቸውና ከ55 አመት በላይ የሆኑ በየአካባቢያቸው ባሉ የጤና ተቋማት መከተብ እንደሚችሉ ተገልጿል።

የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል ስራ ላይ ግንባር ቀደም  ሚና የነበራቸው የሀይማኖት ተቋማት አሁን ላይ እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር ውይይት አድርገዋል።

(በደምሰው በነበሩ)