የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጤና ስርዓቱን ፈተና ላይ መጣሉ ተገለጸ

መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በህብረተሰቡ ላይ የህመም ሆነ የሞት ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ የጤና ስርዓቱን ፈተና ላይ ጥሎታል ተባለ።
ወደ ኢትዮጵያ ከገባ አንድ አመት ያለፈው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ ያስከተለው ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ 11 የሚሆኑ የጤና ማህበራት የቫይረሱን ወረርሽኝ በተመለከተ በጋራ በሰጡት መግለጫ ከቅርብ ወራት ወዲህ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመቀዛቀዛቸው እና ቸል በመባላቸው የቫይረሱ ስርጭት መስፋፋቱን አስታውቋል።
በኮቪድ-19 በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ የጤና ባለሙያውና ስርዓቱ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መሆኑ በገሀድ እየታየ ነው ብሏል።
በህብረተሰቡ ዘንድ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን ለአብነትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አለመጠቀም፣ ርቀትን አለመጠበቅ፣ የእጅ ንፅህና አለመጠበቅ፣ የህመም ምልክት ሲኖር ራስን አለመለየት እና መዘናጋት አሁን ለደረስንበት አሳሳቢ የኮቪድ-19 ስርጭት ዳርጓልም ነው የተባለው።
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ዋና እና ወጪ ቆጣቢ መከላከያ መንገዶች አማራጭ መሆናቸው ታሳቢ ተደርጎ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥርና ህጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሙያ ማህበራቱ አሳስበዋል።
በሌሎች ሀገራት በፍጥነት እየተሰራጨ ነው የሚባልልት አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሊሆን ስለሚችል በጉዳዩ ላይ መንግስት ሳይንሳዊ ጥናት ሊያደርግ እንደሚገባም በመግለጫው ተጠይቋል፡፡
የተጀመረው ክትባትም በተቀመጠለት አሰራር መሰረት በፍጥነት ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጤና ሚኒስቴር በትላንትናው ዕለት ባደረገው ዕለታዊ ሪፖርት መሰረትም እስካሁን 219ሺህ 381 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውና 3ሺህ 25 ዜጎች በቫይረሱ ህይወታቸውን ማጣታቸው ተመላክቷል፡፡ 850 የሚሆኑ ዜጎችም በፅኑ ህሙማን ክፍል እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
(በደምሰው በነበሩ)