የወልድያ ከተማ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ጸጥታ በንቃት እየጠበቁ መሆኑን ገለጹ

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – የአሸባሪውን የትህነግ ሴራ ለማክሸፍ የወልድያ ወጣቶች ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር የከተማዋን ጸጥታ በንቃት እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም እስካሁን ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አለመኖሩን እና የነዋሪው የዕለት ተዕለት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ወጣቶቹ የከተማውን ሰላም ለማስጠበቅና ሰርጎ ገቦችን በመከታተል ለሕግ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የአሸባሪው ትህነግ ቡድን የሚነዛውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ለመመከት ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሐመድ ያሲን የከተማው ወጣቶችና ማኅበረሰቡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እስካሁን ያደረጉት ተግባር ታሪክ የማይረሳው ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን በከተማዋ ሊቃጣ የሚችል የትኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመመከት በሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው አስማሜ ኅብረተሰቡ የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በሚነዛው የሐሰት መረጃ ሳይደናገር የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ኀላፊው አክለውም ነዋሪው የጸጥታ አካሉን የመደገፍ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ሲል የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡