የዓለም የምግብ ደኅንነት ቀን እየተከበረ ነው

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) “ደኅንነቱ የተረጋገጠ ምግብ ለመልካም ጤንነት “በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የምግብ ደኅንነት ቀን እየተከበረ ነው።

ቀኑ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አዘጋጅነት በዓለም ለ4ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡

በየዓመቱ ግንቦት 30 በዋናነት የሚከበረው የዓለም የምግብ ደኅንነት ቀን የምግብ ወለድ አደጋዎችን ለመከላከል፣ ለመለየትና ለመቆጣጠር እንዲሁም የሰውን ጤንነት ለማሻሻል መሆኑ ተነግሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት በዓመት የ420 ሺሕ ሰዎች ህይወት ያልፋል፡፡

የምግብ ደኅንነት ችግር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰል ቀውሶችን የሚያስከትል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ሳቢያ በርካታ ዜጎች ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ተጠቂ እየሆኑ ነው ተብሏል፡፡

ጤናማ የሆነ አምራች ዜጋ ለመፍጠር በምግብ ደኅንነቱ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

በዙፋን አምባቸው