የጂቡቲው ምርጫ ድምፅ መስጠት ተጀመረ

የጂቡቲው ምርጫ
ሚያዝያ 01/2013 (ዋልታ) – በጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ለአምስተኛ ጊዜ የሚወዳደሩበት ምርጫ ዛሬ ድምፅ መስጠት ተጀምሯል፡፡
ከአረብ ሊግ የተወከሉ የምርጫው ታዛቢ ሁሉም ነገር በሰላም እየተካሄደ ነው ሲሉ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
ከ200 ሺህ በላይ ድምፅ ሰጪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ምርጫ ምሽት ላይ ይዘጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ዋና ዋና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው የማስመሰል ምርጫ ነው በሚል ጥለው መውጣታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ብቸኛ ተፎካካሪያቸው ዘካሪያ ኢስማኤል እምብዛም የማይታወቁ ነጋዴ ሲሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ አባል እንደነበሩ ዘገባው አስታውሷል፡፡
ተፎካካሪያቸው የፅዳት እቃዎችን ከውጪ አገራት የሚያስገቡ ሲሆን፣ ባለፈው ጥር ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ይፋ እስከሚያደርጉ ድረስ በሕዝቡ ዘንድ የሚያውቃቸው አልነበረም ነው የተባለው፡፡
የ57 አመት ጎልማሳው ለጉሌህ ስጋት እንደማይሆኑ እና ፕሬዘዳንት ጉሌህ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል፡፡
በስትራቴጂያዊ አቀማመጧ ለቀጠናው ቁልፍ ከሚባሉ አገራት መካከል የሆነችው ጂቡቲ ከአንድ ሚሊየን የሚያንስ ህዝብ ያላት ሲሆን፣ አሜሪካ እና ቻይናን ጨምሮ የሃያላን አገራት የወታደራዊ መቀመጫ መሆኗ ይታወቃል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ለ22 አመታት አገሪቷን አስተዳድረዋል፡፡