የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፕሮጄክት ለ7.4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ሐሳብ አመንጭነት በተቀረጸው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፕሮጀክት ለ7 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥርና 12 ሺህ 500 በላይ የውጭ ባላሃብቶች ማስተናገድ እንደሚችል ተገለጸ፡፡

ፕሮጄክቱ መልክዓምድራዊ አቀማመጥን በመጠቀም ኢትዮጵያ እና ምስራቅ አፍሪካን ተጠቃሚ የሚያደርግ እቅድ ሲሆን በውስጡም አስር የውጭ ገበያ የሚፈጥሩ እና ስድስት የሃገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት የሚሰሩ የማምረቻ ተቋማት እንዳሉት የፕሮጄክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ገልጸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ዞኑ በአዳማ እና ሞጆ አካባቢ በሚገኝ 23 ሺህ 656 ነጥብ 51 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን በአካባቢው ለሚገኙ 33ሺህ ሰዎች የጋራ ተጠቃሚ እዲሆኑ የሚያደርግ ህግ መጽደቁንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ግብዓቶችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ያለውን የስራአጥ ቁጥር ለመቀነስ፣ የውጭ ግብይትን እና የውጭ ምንዛሬን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም አዲስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሃገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን ጨምሮ ሚኒስቴሮች እና የውጭ አጋር ድርጅቶች በፕሮጄክቱ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

የኢኮኖሚ ዞኑ በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ‹‹መገለታ ኦሮሚያ›› ቀርቦ የጸደቀ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በቀጣዮቹ 40 ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በአፍሪካ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

(በትዝታ መንግስቱ)