የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ጩኸቶች ቢኖሩም የግድቡ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ይጠናቀቃል- ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ

ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ጩኸቶች ቢኖሩም የግድቡ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስና መምህርና የህዳሴው ግድብ የድርድር አባል ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ ገለጹ።

የአገር ውስጥ አንድነትን በማጠናከር እና ሰላምን በማረጋገጥ ሁሉም የግድቡ ዘብ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከጣለችበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ ጊዜያት ከግብጽና ከሱዳን በኩል ጩኸቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሮፌሰር ይልማ፣ አሁንም ጩኸት አለ፤ የግድቡ ግንባታም እየተከናወነ ነው፣ በተያዘለት ጊዜም ይጠናቀቃል ብለዋል።

ሀገራቱ የሚጮሁት የግድቡ ግንባታ በነሱ ላይ የሚያስከትለው አደጋ ወይም ሊፈጥር የሚችለው ስጋት ስላለ ሳይሆን፤ ቀደም ብሎ የነበረውንና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመውን ኢ-ፍትሀዊ የውሀ ክፍፍል ለማስቀጠል ካላቸው የጸና ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ግብጽና ሱዳንን እ.ኤ.አ የ1959 የደረሱበት ስምምነት በውሃው ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም እንዲይዙ እንዳደረጋቸው አስታውቀው፣ ስምምነቱም ሆነ ከስምምነቱ ተነስተው የያዙት አቋም ኢ-ፍትሐዊ እንደሆነ አመልክተዋል።

ሀገራቱ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ከጅምሩ አንስቶ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ግድቡ ግን በተያዘለት ጊዜ ይጠናቀቃል ያሉት ፕሮፌሰር ይልማ፣ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንደሚከናወንና ከሙሌቱ በኋላም የሚመጣ  ነገር እንደማይኖር አስታውቀዋል።

ግብጽ ግድቡ ላይ ጉዳት ለማድረስ ብትሞክር ዘላቂ ኪሳራ ውስጥ እንደምትገባ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ይልማ፣ የታችኛው ተፋሰስ አገር የውሃ ተጠቃሚ ሆኖ የላይኛው ተፋሰስ አገር ላይ ጦርነት አይጀምርም፤ ቢጀምር የሚደርስበትን ጉዳት ያውቀዋል ብለዋል።

ግብጽ ልታደርግ የምትችለው ፉከራ እና ማስፈራራት፣ በተቻላት ደግሞ ግንባታውን ማስተጓጎል እንደሆነ አመልክተው፣ የውጪ ስጋቶችን ለመቀልበስ መፍትሔው የውስጥ ሰላማችንን ማረጋገጥ ነው፤ ይህም በሁላችንም እጅ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአገር የውስጥ ሰላም መረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ድንበር ላይ ጠላት እየፎከረ እርስበርስ መናቆር አገርን ማስደፈር ነው ያሉት ፕሮፌሰር ይልማ፣ የውጭ ጠላት የሚፈልገው ይህንን እንደሆነና ሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች ግድብን መጨረስ አትችልም ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል።

በመገናኛ ብዙኃኖቻቸው የሚያጋግሉት የውስጥ ብጥብጥ እንዲኖር ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ይልማ፣ የውጭ ጠላት ‹‹ጦርነት እከፍታለሁ›› እያለ ሲያስፈራራ፤ የአገር ውስጥ አንድነትን ማሳየት ዋነኛው ስትራቴጂ ነው፤ ሁሉም ህዝብ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሊነቃ እንደሚገባ አመልክተዋል።

‹‹ከድህነት መውጫው መንገድ ጫፍ ላይ ነን›› ያሉት ፕሮፌሰር ይልማ፤ የአገር ውስጥ አንድነትን በማጠናከር እና ሰላምን በማረጋገጥ ሁሉም የግድቡ ዘብ መሆን እንዳለበት ማሳሰባቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።