የጥጥ መዳመጫው…

የጥጥ መዳመጫው…
(በአመለወርቅ መኳንንት)
—————————————-
እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን የሆነ የማንነት መገለጫ ያለን የቱባ ባህል ባለቤቶች ነን፡፡ እኛ ሀበሾች የራሳችን የሆነ የባህላዊ እሴቶች፣ ወግና ልማዶች፣ የሰላምታ አለዋወጥ ስርዓት፣ የአለባበስ ስርዓት፣ ጨዋታ፣ ስነቃል፣ ሃይማኖት፣ እምነት፣ ጋብቻ፣ እንዲሁም የኪነጥበብና የእደጥበብ፣ የጌጣጌቶች፣ የሁሉም ባለቤቶች ነን:: ታዲያ ይህን የማንነት መገለጫ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸን ወግና ክብሩን እንደጠበቀ ሳይከለስና ሳይበረዝ ነው የተረከብነው፡፡
ዘመን ተሻጋሪ ታሪክን መሰረት ያደረገ የጋራ ዕሴት የገነባንና በልዩነት መካከል ያለንን ውበትና አንድነት የሚያጎላ፣ የዘመናት ታሪካችንና ባህላዊ ትስስራችንን የሚያሳይ በእውነተኛና ጠንካራ አንድነት ላይ የተቆራኘ የባህላዊ ትውፊት ባለቤቶች ነን፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን ይህን ባህልና ትውፊታችንን አክብረን የያዝነው አይመስልም፣ ዋጋውን እያሳነስነው እንገኛለን፡፡ “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” ሆኖብናል ነገሩ፡፡ በተለይ በተለይ የመከባበርና የመደማመጥ ባህላችን እየጠፋ ይገኛል፡፡
ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝን ሐሳብ መነሻ አድርጌ ልጀምር፡፡ በአንድ ወቅት አንድ በእድሜ ገፋ ያሉ አባት ከእግራቸው እስከ እራስ ፀጉራቸው ነጭ የለበሱ፣ ግርማ ሞገስ የሆነ ፀጉራቸው የተነደፈ ጥጥ የሚመስል፣ በቀኝ እጃቸው ምርኩዝ የጨበጡ፣ በግራ እጃቸው ነጭ ጭራ የያዙ አባት በዕለተ ሰንበት ከቤተክርስቲያን አረፋፍደው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በመንገድ ላይ አንድ ከሰውነቱ ፈርጠም፣ ከቁመቱ ዘለግ፣ ዓይኖቹ ጎላ ጎላ ብለው ቀላ ያሉ መልከ መልካም ወጣት በመንገድ ላይ አገኛቸውና እኝህን አባት ከታች እስከ ላይ በመገረም አያቸው፡፡ አዛውንቱም የወጣቱ ትኩር ብሎ ማየት አስገርሟቸው መንገዳቸውን ሲቀጥሉ ድንገት ወጣቱ፣
“እኔ እምልዎት አባ? አላቸው ሽማግሌውም
“አቤት የኔ ልጅ” አሉ ትህትና በተላበሰ አነጋገር፣
“የሆነ ቦታ ጠፍቶኝ ነበር ያውቁታል ልጠይቅወት?” አላቸው ፀጉሩን በግራ እጁ እየፈተለ፣ ከንፈሮቹን በምላሱ እያረጠበ አይኖቹን አንዴ ወደ ግራ አንዴ ወደ ቀኝ እያደረገ፣
“ካወኩት ምን ገዶኝ የኔ ልጅ ጠይቀኝ” አሉት:: አሁንም ወጣቱ ከላይ እስከ ታች ከፍ ዝቅ አድርጎ እያያቸው፣
“የጥጥ መዳመጫው የት አካባቢ ነው?” አላቸው አዛውንቱም የልጁ ጥያቄ የእውነት ጥያቄ ሳይሆን የአሽሙር ስድብ መሆኑ ገብቷቸው በመገረም ስሜት ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ ትኩር ብለው አዩትና፣
“የኔ ልጅ በቀኝ በኩል ወደ ፊት ስትሄድ ታገኘዋለህ፡፡ ነገር ግን በዚህ አካሄድህ አትደርስበትም” አሉት ውስጣቸው በሀዘን ተሞልቶ፡፡
ትልቅ ሰው ክቡር፣ ንግግሩ የሚደመጥ፣ ቁጣው የሚፈራ፣ ምክሩ የሚያስታርቅ ነው፡፡ ትውልዱ የሚያዳምጥ፣ የሚከባበር እንዲያዳምጥ፣ ነገን ናፋቂ፣ ሀገሩን ወዳጅ ሊሆን ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር ወዳድ አርበኞች እናት ሀገራቸውን ከውጭ ጠላት ለማዳን፣ ለሕዝቦች ክብርና ዘላቂነት፣ ለባህል፣ ለኃይማኖት፣ ማንነትን ለማስጠበቅ ተጋድለውበታል፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ ኢትዮጵያን ማዳን የሕዝቡን ባህል፣ ክብሩን፣ ማንነቱን፣ ጀግንነቱን ማስጠበቅና ባህላዊ እሴቶችን ወግና ልማዶችን ማስቀጠልና ከባርነት ማዳን ነው። ዳሩ ግን ጀግኖች አባቶቻችን የወደቁ የተነሱለትን ብሎም የህይወት መስዋዕት የከፈሉለትን ማንነት፣ ባህል፣ ትውፊት እና እምነትን ከማስጠበቅ ይልቅ “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ ” እያስባለን ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ግሎባላይዜሽንን መሰረት በማድረግ ለአሉታዊ የባህል ወረራ ሰለባ ስር እየሰደደ ነው፡፡ ባህል በመወራረስ የሚገኝ ቢሆንም አንዳንዱ ባህል ለአጭር ጊዜ እንደ ፋሽን ብቅ ብሎ እልም የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ እንደ ሀይማኖት ለብዙ ዘመናት የሚቆይ ይሆናል፡፡
ነገር ግን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በተለይ ተስፋ የተጣለበት ወጣቱ ትውልድ ግን በተለያዩ ሱሶችና በጎጂ መጤ ባህሎች አሉታዊ ተጽዕኖ ስር በመውደቅ ለማህበራዊ፣ ስነልቦናዊና አካላዊ ችግሮች ከመጋለጥም ባሻገር ስለ ሀገሩ ባህል፣ ታሪክና ትውፊት ጀርባውን ሰጥቷል፡፡
በተለይ ህብረተሰቡ ትኩረት ያልሰጣቸው ወይም ልብ ያላላቸው ባህሎችና ልምዶች በሀገራችን ተስፋፍተዋል፡፡
ለአብነትም “ፍሪ ዞን፣ ፍሪ ሳተርደይ እና ኖ ሼም ግሩፕ” በሚል ወጣቶች በቡድን የሚፈፅሟቸው መጤ እና ጎጂ ልማዶች በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክልሎች በስፋት እንደሚስተዋሉ ኢዜአ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን የ2009 ዓ.ም ጥናቶች ዋቢ አድርጎ በዘገባው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከሁሉም አስቀድሞ ግን የምዕራባውያን ባህል ከመውረሳችን በፊት ከሀገሪቱ ሕጎች፣ ባህሎች፣ እምነቶች፣ እና ማንነቶች ጋር ያለውን ዝምድና በቅድሚያ ማስተዋልና እና ማጤን ይገባል፡፡
ምክንያቱም ለምዕራባውያን መልካም የሆነ ባህል ሁሉ ለኢትዮጵያውያን መልካም ነው ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብን ዘመናዊ ባርያ የሚያደርጉ መጤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባህሎችን በጋራ ልንታገል ይገባል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን በባህላችን የሚደነቁ የራሳችን የቅኔ አደባባይ፣ የዜማ መዲና፣ የንግግር ስልት ያለን ኩሩ ህዝቦች ነን፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ጾታና እድሜ ሳይለዩ የማነው ልጅ ሳይሉ በመንገድ ላይ ጥፋት ሲያጠፋ የተገኘን ህፃን ልክ እንደ ልጃቸው ቀጥተው ገስፀው፣ መክረው እና ዘክረው ነበር የሚሄዱት ወላጅም “ለምን ልጄን ቀጣኸው? ለምን ተቆጣኸው?” አይልም እንዲያውም “ደግ አደረክ” ብለው ምስጋና ይቸሩ ነበር፡፡
የሀገራችንን መልካም እሴቶችና ባህሎች ከመጤ ባህል ወረራ በመጠበቅ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል፡፡ ታሪኩን፣ እምነቱን፣ ባህሉንና ማንነቱን የረሳ ትውልድ በራሱ ተማምኖና ኮርቶ አገሩን ሊጠብቅና በጋራ ሊገነባ ይችላልን?
ቸር ይግጠመን!