የካቲት 14/2014 (ዋልታ) መነሻውን ጋምቤላ ክልል ያደረገ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ የጦር መሳሪያውን በሳጥን ደብቆ ለአሸባሪው ሸኔ ለማቀበል ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ክትትል ሲደረግበት የቆየው ግለሰቡ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ አንድ ብሬን በፍራሽ ጠቅልሎ በመጫን የካቲት 12 ቀን 2014 ከቀኑ 7:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ መግባቱ ነው የተገለፀው።
ግለሰቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ በማቅናት ሳጥን በማሰራት የጦር መሳሪያውን ባሰራው ሳጥን ውስጥ መሸሸጉም ተጠቁሟል።
መዳረሻውን ኦሮሚያ ክልል ሆለታ ከተማ በማድረግ የጦር መሳሪያውን ለሸኔ የሽብር ቡድን ለማቀበል ሲሞክር በተደረገበት ክትትል ሱሉልታ ከተማ ላይ በኦሮሚያ ፖሊስ እጅ ከፈንጅ መያዙ ነው የተገለፀው።