የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ሆነ

ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ሆነ።

በስትራቴጂካዊ ዕቅድ ላይ የፌዴራልና ክልል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የፖሊስና ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች፣ የማረሚያ ቤት፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች የፍትሕ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የሚተገበረውን ዕቅድ አድቫንስ አሶሴሽን ኮንሰልታትን በተሰኘ የግል ድርጅት አማካሪነት የተዘጋጀ ነው።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፍርድ ቤቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሶስት ግቦችን በማስቀመጥ ሲሰሩ ቆይተዋል።

አንደኛው የዳኝነት ነፃነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት ሲሆን፣ ሁለተኛው የዳኝነት ቅልጥፍና ተደራሽነት ሲሆን ሶስተኛው ግብ ደግሞ ለዳኝነት አገልግሎት አስተዳደራዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሆነ ተናግረዋል።

“ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ የሚተገበረው ስትራቴጂክ ዕቅድም እነዚህን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል” ብለዋል።

የፍርድ ቤቶቹ የለውጥ ራዕይም በነዚህ ምሰሶች ላይ እንደተመሰረተ  ወይዘሮ መዓዛ ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ “ይህም የሕግ የበላይነትን፣ የመንግስትን ቅቡልነት ያስተናግዳል፤ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ነጻ፣ገለልተኛና ተዓማኒ ፍርድ ቤቶች መገንባት የዴሞክራሲ ሂደቱን ለመቅረጽ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ይህ ከሆነ ‘ለአገራችን የምስራች ነው’ ብለዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ፍርድ ቤቶች በቅልጥፍና፣ በውጤታማነትና ሰው ተኮር ሆነው በነጻነትና በገለልተኝነት እንዲሰሩ ርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።

የዕቅዱ ራዕይ የህዝብ አመኔታ ማግኘት ነው ያሉት ወይዘሮ መዓዛ፤ ይህ ደግሞ የማያቋርጥ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ካልሆኑ ከሚፈለገው የቅልጥፍናና ውጤታማ የፍትህ ሥርዓት መድረስ እንደማይቻልም ገልጸዋል።

ዳኞች በነጻነት እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ የዳኞች ነጻነትም ከተጠያቂነትና ኃላፊነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንስተዋል።

ፍርድ ቤቶች ድምፅ ለመስጠት ጥቂት ቀናት የቀረውን ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ለሚመጡ ክርክሮች ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ ብቁ ውሳኔ ሰጭ ሆነው እንደሚያገለግሉ አረጋግጠዋል።

መንግሥት፣ ፓርቲዎችና ሕዝቡም በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት ሊያሳድሩባቸው ይገባል ብለዋል።

የአድቫንስ አሶሴሽን ኮንሰልታት የግል ድርጅት ተወካይ አቶ ዮሴፍ እንደሻው በተለይም እንደተናገሩት ስትራቴጂክ ዕቅዱ የተዘጋጀው ዝግጅት ከፍርድ ቤቶች፣ ከማረሚያ ቤቶችና ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት መረጃ በማሰባሰብና ከተተነተነ በኋላ ነው።

የዕቅዱ ዋና ግቦች የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቀላጠፈ፣ ተደራሽና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል፣ ነጻና ገለልተኛ ዳኝነት አገልግሎት ማረጋገጥ ነው ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።