የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን መከሰስ የፓርቲያቸው አባላት ጭምር እየደገፉ ነው

ፕሬዝዳናት ዶናልድ ትራምፕ

 ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥቂት ቀናት ከቀረው ሥልጣናቸው ለማባረር የሚያደርጉት ጥረት ከሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ድጋፍ እያገኘ መሆኑ ተነገረ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሥልጣን እንዲባረሩ የሚጠይቀው ክስ እንዲመሰረትባቸው ድጋፋቸውን ከገለጹት መካከል በተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛዋ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴ ሊዝ ቼኒ፤ ባለፈው ሳምንት ዋሺንግተን ውስጥ ከነበረው ግርግር ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ ድምጽ እንደሚሰጡ በይፋ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሳምንት ያህል ድምጻቸውን አጥፍተው ከቆዩ በኋላ ማከስኞ ምሽት በሰጡት ቃል ደጋፊዎቻቸው በአገሪቱ ምክር ቤት ላይ ለፈጸሙት ጥቃት ኃላፊነቱን እንደማይወስዱ ገልፀዋል።

የዛሬ ሳምንት በአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት የሚተኩት ዶናልድ ትራምፕን ከቀሯቸው የሥልጣን ቀናት በውርደት እንዲባረሩ ዲሞክራቶች ግፊት እያደረጉ ነው።

የአገሪቱ ምክር ቤት በፕሬዝዳንቱ ላይ አመጽ በማነሳሳት በሚቀርብባቸው ክስ ላይ በዛሬው ዕለት ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዚህም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ በስልጣን ዘመናቸው ሁለት ጊዜ የተከሰሱ መሪ ይሆናሉ።

የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዲክ ቼኒ ሴት ልጅ የሆኑት ሊዝ ቼኒ ባወጡት መግለጫ ላይ ትራምፕ “በሕገ መንግሥቱና በገቡት ቃል ላይ ክህደት ፈጽመዋል” ብለዋል።

የዋዮሚንግ ግዛት ተወካይ የሆኑት ሊዝ ጨምረውም ፕሬዝዳንቱን “አመጸኞቹን ጠርተው በማሰባሰብ የጥቃቱን እሳት ለኩሰዋል” ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ሁለት ተጨማሪ የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ አባላትም በትራምፕ ላይ የሚከፈተውን ክስ በመደገፍ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ የሆኑትና የትራምፕ ወዳጅ ኬቭን ማካርቲ ክሱን እንደሚቃወሙት የገለጹ ሲሆን፣ የፓርቲያቸው አባላት በሙሉ በምክር ቤቱ ውስጥ የተቃውሞ ድምጽ እንዲሰጡ ጥሪ እንደማያደርጉ ገልጸዋል።

ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ የሆኑት ሚች ማኮኔል ለቅርብ ሰዎቻቸው ተናገሩት ብሎ እንደዘገበው፣ ፕሬዝዳንቱን በዲሞክራቶች መከሰሳቸው ትራምፕን ከፓርቲው ለማስወገድ ይረዳል ብለው እንደሚያምኑ አመልክቷል።

ማኮኔል ለተባባሪዎቻቸው ጨምረው እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሊያስከስስ የሚችል ጥፋት ፈጽመዋል ብለው እንደሚያምኑ ዋሽንግተን ፖስት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።