የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩቲዩብ ታገደ

 ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ከታዋቂዎቹ የማህበራዊ ትስስር መድረኮች መካከል አንዱ የሆነው ዩቲዩብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የድርጅቴን ደንብ ጥሰዋል በሚል ማገዱ ተገለጸ።

በጎግል ባለቤትነት የሚተዳደረው ዩቲዩብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አዳዲስ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዳይለጥፉ ወይንም ደግሞ በቀጥታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዳያጋሩ ለሰባት ቀን ያህል ማገዱን ያስታወቀ ሲሆን፣ እግዱ ከዚህም ረዘም ያለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

ኩባንያው የዶናልድ ትራምፕን ገጽ፣ የድርጅቱን አመጽን አለማነሳሳት የሚለውን ደንብ ጥሷል ሲል ተናግሯል።

ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ማታ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያጋሩ ሲሆን፣ የተወሰኑት አሁንም በሰሌዳቸው ላይ ይገኛሉ።

ዩትዩብ ባገዳቸው የዶናልድ ትራምፕ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ውስጥ ምን እንዳሉ የጠቀሰው ነገር የለም።

ይህ ውሳኔ የተሰማው የተለያዩ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፕሬዝዳንቱ ከዩቲዩብ እንዲታገዱ የሚጠይቅ ማስታወቂያ ለመልቀቅ ከዛቱ በኋላ ነው።

ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንቱ ከፌስቡክ እንዲታገዱ ሲቀሰቅስ የነበረው ጂም ስቴየር ዩቲዩብ የፕሬዝዳንቱን ቻናል እስከመጨረሻው በመዝጋት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

“እስከወዲያኛው ይዘጉታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለትራምፕ እዚህ መድረስ ግጭትን መቀስቀሱ በጣም አሳዛኝ ነው፣ ነገር ግን ዋነኛ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል” በማለት ከእገዳው በኋላ በትዊተር ሰሌዳው ላይ ለጥፏል።

ጎግል እንዳለው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ገጻቸው ከዚህ በኋላ የድርጅቱን ፖሊሲ የሚቃረን ጥፋት ሰርተው ከተገኙ እስከ መጨረሻው የሚታገዱበት እድል አለ።

ድርጅቱ እንዳሳወቀው ትራምፕ አመጽን በማነሳሳት ይህ የመጀመሪያ ጥፋት ሆኖ የተመዘገበባቸው ሲሆን፣ ዳግመኛ ተመሳሳይ ሁለት ጥፋቶች ከተመዘገበባቸው እስከ ወዲያኛው ከገጹ ላይ ይሰናበታሉ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በካፒቶል ሂል የነበረውን አመጽ ተከትሎ ቢያንስ ጆ ባይደን ስልጣን እስኪረከቡ ድረስ ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም ታግደዋል።

ትዊተር በበኩሉ በቋሚነት የፕሬዝዳነቱን አካውንት አግዶታል።

አማዞን ትዊች ገጻቸውን እንዳይሰራ ያደረገ ሲሆን፣ ስናፕቻት በበኩሉ ዘግቶባቸዋል።

ሾፒፋይ፣ ፒንትረስት፣ ቲክቶክ እና ሬዲት ፕሬዝዳንቱ ለተከታዮቻቸው በሚያጋሩት መረጃዎች ላይ ገደብ መጣሉን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል።