ዩኒቨርሲቲዎች የውይይትና የሐሳብ ፍጭት የሚከናወንባቸው ተቋማት ሊሆኑ ይገባል – የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

“የሰላም ወግ፣ ብሄራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ ዕድገት” በሚል በወራቤ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ቶፊቅ ጀማል ዩኒቨርሲቲዎች የውይይት እና የሀሳብ ፍጭት የሚከናወንባቸው መሆን ሲገባቸው፣ የግጭት ማዕከል በመሆን አለመረጋጋት ሲስተዋልባቸው ቆይቷል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በዩኒቨርሲቲዎች ለነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ዋነኛ መንስኤ የማንነት ፖለቲካ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መድረኩ ዩኒቨርሲዎች ለተቋቋሙበት አላማ እንዲቆሙ፤ የሀሳብ እና የውይይት ማዕከል ሆነው እንዲቀጥሉ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል? በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ጽጌሬዳ ወልደብርሃን ሴቶችን ያሳተፉ የሰላም ሂደቶችን መከተል ስኬታማ ውጤት እንዳለው ገልጸው፣ መግባባት ላይ እንዲደረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ፣ የሰላም ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሁም የስልጤ ዞን አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

(በደረሰ አማረ)