ይቻላልን ለአፍሪካውያን ያስተማረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የዓባይ ወንዝ ከኤፍራጠስ እና ጤግሮስ ወንዞች ጋር አብሮ የሚወሳ ታሪካዊ ወንዝ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ወንዝ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ በመገንባት ላይ ያለ በኢትዮጵያ ምድር ታሪካዊው እና ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ወዲህ እነሆ አስር ዓመታትን አስቆጠረ፡፡
የህዳሴው ግድብ የታላቅ ህዝብ የአንድነት ተምሳሌት የሆነ የአይቻልም መንፈስን ሰብሮ ይቻላልን ያነገሰ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ አሻራ ያረፈበት ቅርስ፣ የመጪ ትውልድ ውርስ ነው፡፡
ይህ ታሪካዊ ግድብ ከህፃን እስከ አዋቂ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እጅ ለእጅ ያያያዘ የአንድነት ማጠንከሪያ ገመድ፣ የኢትዮጵያውያን የእድገትና ብልፅግና፣ የተስፋ ብርሃን ነው፡፡
ይህን ተስፋ ለማሳካት መላ ኢትዮጵያውያን ያለምንም የብሄር፣ የጾታ እና የእምነት ልዩነት በሁሉም መስክ አኩሪ ድጋፍ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙሃን፣ አርቲስቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም ጋር በመሆን የንቅናቄ ሥራው ከጫፍ እስከ ጫፍ አስተጋብቷል፡፡
እናት ከመቀነቷ፣ አባትም ከቤተሰቦቹ የዕለት ጉርስ በመቀነስ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ ከሀገር ውስጥ እስከ ሀገር ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ በመረባረብ የተነሱለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እነሆ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ታላቁን የህዳሴ ግድብ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግን ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ እና ህልም ለማሳካት ብዙዎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የግል ህይወታቸውን ወደ ጎን በመተው ለግድቡ ስኬት ታትረዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ ራስ ወዳድ አካላት የሀገርን ሀብት እና ንብረት ለግል ጥቅማቸው ለማዋል የህዳሴ ግድቡን ለማስተጓጎል ያልተገባ ክህደት ለመፈፀም የሞከሩ አካላትን የበሉበትን አገር ወጪት ሰባሪነታቸውን ታሪክ መዝግቦታል፡፡
ነገር ግን ሀገራዊ ለውጡ እውን ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት እውነታውን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ግድቡ በኢትዮጵያውያን የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው በመደረጉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የህዝቡ ንቅናቄ ተጠናከሮ ቀጥሏል፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ከአፍሪካ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ፣ ኤዥያ እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ከሌሎች የዓለም አገራት በርካታ ዲፕሎማቶች እና ጎብኝዎች ታድመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ዓለምአቀፋዊ እና ሉዓላዊ መብቷን በተመለከተ ለአለም ክፍል ግልጽ የማድረግ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን በመጠቀም ሀይል ለማመንጨት የዓባይ ውሃን በፍትሃዊና እኩልነት መርህ ለልማት ለማዋል ጠዋት ማታ ደፋ ቀና እያለች ባለችበት ወቅት በተለያዩ መንገዶች የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የኢትዮጵያ እድገትና ልማት እውን እንዳይሆን የሚሹ አገራትም እጣታቸውን በመቀሰር ድማፃቸውን ማሰማት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
ግብፅና ሱዳን ለብዙ ዘመናት የዓባይን ውሃ ብቻ ሳይሆን አፈሩንም ተጠቅመዋል፤ ነገር ግን ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ የሌለች አገራት ጣልቃ ገብነት ታክሎበት የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰነዘሩት አወዛጋቢ አስተያየት ለድርድሩ እንቅፋት ከመሆኑም አልፎ ጸብአጫሪነትና በሀገራት መካከል ግጭትን የሚያበረታታ የአገራቸውን ህዝብ የማይወክል ንግግር ነበር የሰነዘሩት፡፡ “ግድቡን ግብጽ በቦምብ ትደረምሰዋለች” የሚለው እብሪት የተሞላበት ንግግር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
ከዚህ ኃላፊነት ከጎደለው አስተያየት በመቀጠልም ግብጽና ሱዳን እርስ በእርሳቸው በሚያሴሩት ሴራ የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚፈጥሯቸው ምክንያቶችና ችግሮች የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግድቡ በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ከማድረጉም በላይ ቁጣንም ያጫረ ሆኗል።
ሆኖም ይህ ጫና ያልበገራት ኢትዮጵያ በመንግሥት እና በህዝቦቿ ድጋፍ ብርሃንን በተስፋ ለሚጠብቁት ህዝቦቿ ለማድረስ የግድቡ ግንባታ በተፋጠነ እና በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ አምባሳደር በመሆን አገሪቱ በፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ግድቡን እየገነባች መሆኗን ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ ለእናት ሀገራቸው ዘብ ቆመዋል፡፡
ምክንያቱም ለዘመናት የዓባይ ወንዝ በበራቸው እየፈሰሰ በከሰልና በማገዶ ጭስ መከራቸውን የሚያዩ በድህነት ያሉትን ኢትዮጵያውያንን የሚታደግ እና የዘመናት የኤሌክትሪክ ሀይል ጥያቄን ምላሽ የሚሰጥ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ታሪካዊ ግድብ ነው፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ 14 ነጥብ 98 ቢሊየን ብር የሚሆነው በህዝቡ ተሳትፎ ተሰብስቧል፡፡
የህዳሴው ግድብ ወቅታዊ የግንባታ ሂደት 79 በመቶ የደረሰ ሲሆን የግድቡ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛው ዙር የደን ምንጣሮው በ”ጂፒኤስ ቴክኖሎጂ” በመታገዝ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌትም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የማይከናወንበት አንዳችም ምክንያት እንደማይኖር መገለጹ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በታታሪ ሕዝቦቿ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠናቅቃ ድህነትን ድል በመንሳት የይቻላልን መንፈስ ለአፍሪካውያን በተግባር የምታሳይበት ጊዜ ቅርብ ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!
(በአመለወርቅ መኳንንት)