ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው

መጋቢት 25/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማእከል ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው።
በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከል ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሳምንት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ማብራሪያቸው ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል በኩል በኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ እውን መሆኑን አንስተው ነበር።
በቴክኖሎጂውም በሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂ አማካይነት ደመናን ወደ ዝናብ በመቀየር በጎጃም እና ሸዋ አካባቢዎች ማዝነብ መቻሉን ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ከሕዝብ ቁጥር እና የእርሻ መሬት ፍላጎት መጨመር ጋር በተያያዘ ደረቅ አካባቢዎችን ለምና ምርታማ ለማድረግ ቴክኖሎጂው ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አብራርተው በቅርቡ ደግሞ በይፋ እንደሚከናወን መናገራቸው ይታወሳል።
በመሆኑም በዛሬው እለት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከል ቴከኖሎጂውን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በፕሮግራሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን በዓለም ከ56 አገራት በላይ ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆኑን ኢዜአ በዘገባው አስታውቋል።