ዶክተር አርከበ ዕቁባይ ለተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተርነት ከአፍሪካ ብቸኛ እጩ ሆነው ቀረቡ

ዶክተር አርከበ ዕቁባይ

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – ዶክተር አርከበ ዕቁባይ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲወዳደሩ ብቸኛው አፍሪካዊ እጩ በማድረግ በሙሉ ድምጽ መምረጡን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አስታወቀ።

የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት 38ኛ መደበኛ ስብሰባ በየካቲት 24 እና 25/2013 ዓ.ም ባደረገበት ወቅት የኢትዮጵያን ወክለው ለተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ተፎካካሪ የሆኑትን ዶክተር አርከበ ዕቁባይን በብቸኛ አፍሪካዊ እጩነት አጽድቋል፡፡

ዶ/ር አርከበ ባለፉት ሰላሳ አመታት ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማትና ቀጣይነት ላለው ሁሉን አቀፍ መዋቅራዊ ሽግግር የሚያግዙ ፖሊሲዎችን በማውጣትና በማስተግበር ስኬታማ እንደሆኑ ህብረቱ ገልጿል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ አባላት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅቱ በብቁ ዋና ዳይሬክተር መመራት እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተው የተወያዩ ሲሆን፣ ዶ/ር አርከበ ካላቸው የስራ ልምድ አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስኩ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጡ ባለሙሉ እምነት በመሆናቸው እጩነቱን አጽድቀውታል ተብሏል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።