ጀርመን ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ለሚያደርግ የታዳሽ ሃይል ልማት ድጋፍ ልታደርግ ነው

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) ጀርመን በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ለሚያደርግ የታዳሽ ሃይል ልማት የሚውል 116 የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገባች፡፡
የገንዘብ ድጋፉ የግል ዘርፉ አፍሪካ ውስጥ በታዳሽ ሃይል መስክ ለሚያደርገው ኢንቨስትመንት የሚያግዝ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የሃይል ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዳንኤል ስክሮት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ጀርመን የምታደርገው ድጋፍ ታዳሽ ሃይልን ለማጎልበት የተያዘውን የ500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ አቅምን የሚያጎለብት ነው።
ጀርመን እያደረገች ያለው እገዛ የፈንዱን መዋእለ ንዋይ 5 መቶ ሚሊየን ዶላር እንደሚያደርሰው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ገንዘቡ የአፍሪካ የታዳሽ ሃይል ተደራሽነትን በማሳደግ የንጹህ ሃይል አቅርቦትን ከፍ ያደርጋል ሲሉም አብራርተዋል።
ድጋፉ እ.ኤ.አ. በ2017 ጀርመን የቡድን 20 አገራት ጉባዔን በሊቀመንበርነት ስትመራ በተደረገ ድርድር የተደረሰ ስምምነት ነው።
ኢትዮጵያን፣ ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ አይቮሪኮስት፣ ግብጽ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ እና ቱኒዝያ ደግሞ ከሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ አገራት መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።