ጀርመን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የፖለቲካ እና የምጣኔሃብት ለውጥ እንደምትደግፍ ገለጸች

ኅዳር 30/2014 (ዋልታ) ጀርመን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የፖለቲካ እና የምጣኔሃበት ለውጥ እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ገለፁ፡፡

የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አውየርን ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እየተገበረች በምትገኘው የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ገለጻ አድርገዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ከልማት ትብብር የምታገኘውን ድጋፍ በተመለከተ ያነሱ ሲሆን፣ ድጋፉ ቀላል የማይባል እና የማይናቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ስቴፋን በበኩላቸው አገራቸው የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኗን አስታውሰው፣ የወከሉት መንግሥት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የፖለቲካ እና የምጣኔሃብት ለውጥ እንደሚደግፍ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የጀርመን መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራርን እንደሚደግፍ በመግለጽ፣ ወደፊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል።