ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ለካንሰር በሚያጋልጥ ምርቱ ምክንያት 700 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፍል ተስማማ

 

ሰኔ 5/2016 (አዲስ ዋልታ) ጆንስን ኤንድ ጆንሰን የተባለው ግዙፉ የመድኃኒትና መዋቢያ አምራች ድርጅት በአሳሳች ማስታወቂያ ለጤና አደገኛ የሆኑ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በማድረስ ተከሶ 700 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።

ክፍያው በህጻናት ዱቄትና በሌሎች ምርቶቹ ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ ኬሚካሎች ምክንያት ከ40 በላይ የአሜሪካ ግዛቶች ለተከፈተበት ምርመራ መቋጫ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።

የኒው ዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሌቲቲያ ጄምስ “አደገኛ ንጥረ ነገር በያዙ የመዋቢያ ምርቶች በማህበረሰብ ላይ ጉዳት ማድረስ ህገ ወጥ ብቻ ሳሆን ጭካኔም ጭምር ነው” ሲሉ አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል።

“በምርቱ የደረሰውን ጉዳት ገንዘብ የሚመልሰው ባይሆንም ተቋሙ ላደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ሆኗል። አደገኛ ምርቶቹም በኒው ዮርክ መሸጫ መደብሮች ድርሽ እንዳይሉ ተደርጓል። ማህበረሰቡን በመጉዳት ጥቅም የሚሰበስቡ፣ ጤናውን የሚጎዱ፣ ህጋችንን የሚጥሱ ሁሉ ቢሮዬ በሙሉ አቅሙ ይታገላቸዋል” ብለዋል ጠቅላይ አቃቤ ህጓ።

በዚህ ስምምነት መሰረትም በኒው ጀርሲ የሚገኘው ፋብሪካ ታልከም ዱቄት ያለባቸውን ሁሉንም የሰውነት መዋቢያ ምርቶች ከዚህ በኋላ እንዳያመርት፣ እንዳያስተዋወቅና እንዳይሸጥ ተከልክሏል።

በፈረንጆቹ 2020 እርጥበትን ለመምጠጥ፣ ሰበቃን ለመቀነስና ጠረን ለመቀነስ የሚያግዘው ታልከም ዱቄት ያለባቸውን ማንኛውንም ምርቶቹን በሰሜን አሜሪካና በአለም ላይ ሽያጭ ማቆሙ አልጄዚራ ዘግቧል።

ያሁኑ የካሳ ክፍያ ስምምነት በምርቶቹ ጉዳት የደረሰባቸው ተጠቃሚዎች በግል ክስ ያቀረቡትን ሰዎች እንደማያካትት የተገለጸ ሲሆን ድርጅቱ ከተከሰሰባቸው 99.7 በመቶ በሂደት ላይ ያሉትን ክሶች በ6 ነጥብ 475 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ለመጨረስ ማሰቡን አስታውቆ ነበር።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ምርቶቹ ችግር እንዳለባቸው እያወቁ መረጃዎቹን ለአስርት ዓመታት ደብቀው እንደነበር የሚዲያ ተቋማት ባደረጉት ምርመራ ማረጋገጣቸው በዘገባው ተጠቅሷል።