ጆ ባይደን የ1.9 ትሪሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ማዕቀፍ ይፋ አደረጉ

                                                  ጆ ባይደን

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተመታውን የአሜሪካ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት 1.9 ትሪሊየን ዶላር የገንዘብ ማዕቀፍ እቅድ ይፋ አደረጉ።

ባይደን ይህን ያስታወቁት በሚቀጥለው ሳምንት በቢሯቸው ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ነው።

ይህ የገንዘብ ማዕቀፍ በምክር ቤቱ ከፀደቀ ለሁሉም አሜሪካዊያን ከሚሰጠው 1 ሺህ 400 ዶላር የገንዘብ ድጎማ ጋር ተደማምሮ ለቤተሰብ የሚሰጠውን 1 ትሪሊየን ዶላር ገንዘብን ያካትታል።

የገንዘብ እፎይታ እቅዱ ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚውል 415 ቢሊየን ዶላር እና ለአነስተኛ ንግዶች ማነቃቂያ 440 ቢሊየን ዶላርንም ይጨምራል ተብሏል።

ዲሞክራቱ ጆ ባይደን በአሜሪካ ከ385 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለውን ወረርሽኝ ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።

ባይደን ባለፈው ዓመት ከሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተሻለ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተሻለ እንደሚሰሩ ቃል በመግባት ዘመቻ አካሂደው ነበር።

የጆ ባይደን የገንዘብ እፎይታ ማዕቀፍ ዕቅድ የመጣው በክረምት ወቅት የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

በአሜሪካ በአንድ ቀን ከ200 ሺህ በላይ አዲስ ሰዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን፣ አንዳንዴ በአንድ ቀን የሟቾች ቁጥር 4 ሺህ እንደምደርስ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡