ጉባኤው ድብቅ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ሃይማኖቶችን ሽፋን በማድረግ ያልተገባ ድርጊት እንዲፈጸም እያደረጉ መሆኑን ገለጸ

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) ድብቅ አላማና ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ሃይማኖቶችን ሽፋን በማድረግ ያልተገባ ድርጊት እንዲፈጸም እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ፡፡

ጉባኤው ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1 ሺሕ 443ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም በጤና አደረሳችሁ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ጉባኤው ባወጣው መግለጫ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር  በሀገሪቱ እየሆነ ስላለው ክፋትና በደል በመጸጸት እውነተኛ ንስሀ በማድረግ ወደ ፈጣሪው በመጠጋት ሊሆን እንደሚገባ ገልጿል።

ግጭት እና ግድያ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው ድብቅ አላማና ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ሃይማኖቶችን ሽፋን በማድረግ ያልተገባ ድርጊት እንዲፈጸም እያደረጉ ሲሆን ለዘመናት ተከባብሮ የኖረውን ሕዝብ አንዱ በሌላው እንዲነሳና አለመተማመን እንዲፈጠር እያደረጉ መሆኑን አመላክቷል።

የዘንድሮውን በዓል ስናከብር ከውጭ ሀገር ወደ ሀገራቸው በመግባት ላይ ለሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ደማቅ አቀባበል ማድረግ እንደሚገባ መግለጫው አስታውሷል።

መግለጫው ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እስልምና በሚያስተምረው መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ያለውን በማካፈል እንዲሆን አሳስቧል።

በወቅታዊ ሁኔታው ተፈናቅለው ከመኖሪያቸው ርቀው በችግር የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ እንዲሆን ጉባኤው በመግለጫው አሳስቧል።