ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ

ሰኔ 26/2016 (አዲስ ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችም ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚገኙበት 36ኛ መደበኛ ስብሰባውን ይካሂዳል፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 55 (17) እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 81 (3) እና አንቀፅ 92 መሰረት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደበኛ ስብሰባው በመገኘት በፌዴራል መንግስቱ የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 55 (11) እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 76 መሰረትም ምክር ቤቱ የ2017 የፌዴራል መንግስት በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አዳምጦ ረቂቅ በጀቱን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በምክር ቤቱ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።