ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ከ5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገነቡ ሁለት መንገዶችን ግንባታ አስጀመሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
የካቲት 28/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ከ5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነቡ ሁለት መንገዶች ግንባታን በስፍራው ተገኝተው አስጀምረዋል።
በአማራ ክልል የሚገነባው ከዱርቤቴ – ቁንዝላ – ሻሁራ – ፍንጅት እንዲሁም ከገለጎ – መተማ ከ5 ቢሊየን 374 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሁለት ምዕራፍ የሚገነባውን 261 ኪሜ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ዚዢያንግ ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ግሩፕ ይሠራዋል ተብሏል።
መንገዱ የአማራ ክልል 3 ዞኖችን ከማስተሳሰር ባለፈ የሀገሪቱ የገቢና ወጪ ምርት ዋና መስመር የሆነውን የመተማ ሱዳን ኮሪደርን የሚያገናኝ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል።
መንገዱ በሶስት ዓመታት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግም ተገልጿል።
የኢቢሲ ዘገባ እንዳመለከተው በግንባታ ማስጀመር መርሐግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ህብረተሠብ ተገኝተዋል።