ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሩሲያውን ልዩ መልዕክተኛ ተቀብለው አነጋገሩ

ጥር 30/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመካከለኛው ምስራቅ እና ምስራቅ አፍሪካ የሩሲያን ልዩ መልዕክተኛ ተቀብለው አነጋገሩ።
የሁለቱ ቀጣናዎች ልዩ መልዕክተኛና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ሚካኤል ቦግዳኖቭ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር እንደተገናኙ ነው በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ በቲውተር ገጹ የጻፈው።

ሁለቱ ወገኖች ትናንት ባደረጉት ውይይት ዘመን ተሻጋሪውን የኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነት በተመለከተ ትኩረት አድርገው መክረዋል።
ልዩ መልዕክተኛው ሩሲያ ለኢትዮጵያ ኅብረት፣ የግዛት አንድነትና ሉኣላዊነት መከበር በመርህ ላይ የተመሰረተውን ድጋፏን ታስቀጥላለች ብለዋል።

አዲስ አበባና ሞስኮ በተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ባለብዙ ወገን ድርጅቶች ላይ በሚኖራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትብብራቸውን ለማላቅ እንደሚሰሩም በውይይታቸው አንስተዋል።

ከሁለተኛው የ“ሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ 2022” ዝግጅት ጋር በተያያዘም ተነጋግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳኖቭ ጋር መወያየታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በዚህም ኢትዮጵያ እና ሩስያ በተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎችም ባለብዙ ግንኙነት መድረኮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር መስማማታቸውን ማሳወቃቸው አይዘነጋም፡፡