ፍትሕ ሚኒስቴር በአገሪቱ የመጀመሪያውን የጥብቅና ድርጅት ፈቃድ ሰጠ

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) የፍትሕ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የጥብቅና ድርጅት (Law Firm) ፈቃድ ሰጠ።

በአዲሱ የጠበቆች አዋጅ አንቀጽ 37 መሰረት የፀና የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ቢያንስ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ጠበቆች አንድ ላይ በመሆን የጥብቅና ድርጅት ማቋቋም እንደሚችሉ የተደነገገ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር መስፈርቱን ለሚያሟሉ አመልካች የጥብቅና ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት የጀመረ ሲሆን በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያውን የጥብቅና ድርጅት ፈቃድ ሰጥቷል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው ፈቃዱን በሰጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥብቅና አገልግሎት በድርጅት መስጠት የሚያስችል ሕግ መውጣቱና ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ለዜጎች የተሻለና ጥራት ያለው የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

አሰራሩ በደንበኞችና ጠበቆች መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን የሚያጎለበት ከመሆኑም ባሻገር የተሻለ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን መግለፃቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW