ፓርቲዎች ባለፉት ምርጫዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጦች አምድ በአግባቡ እንዳልተጠቀሙ ተገለጸ

 

የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ሽፋን

የካቲት 17፣ 2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በተካሄዱት አገር አቀፍ ምርጫዎች ፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ሽፋን በአግባቡ እንዳልተጠቀሙ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።

በባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃን ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ደሬሳ ተረፈ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለጹት፤ ከ1997 ዓ.ም ከተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ አንስቶ ለምርጫ ቅስቀሳ ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ሽፋን ቢመደብም በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል በአግባቡ የመጠቀም ችግር ታይቷል።

ከአጠቃቀም አኳያ የተሻለ የሚባለው በ2007 ዓ.ም ምርጫ የተደለደለው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደሬሳ፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋርና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ አጠቃላይ አጠቃቀማቸው 73 በመቶ እንደነበር አመልክተዋል።

ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በ2002 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ በድምሩ 53 በመቶ፣ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ደግሞ 66 በመቶ ብቻ አጠቃቀም እንደነበራቸው አመልክተዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ዋናው የሚታየው ችግር በተፈቀደላቸው የአየር ጊዜና የአምድ ሽፋን አለመጠቀም መሆኑንም አመልክተዋል።

የአየር ሰዓት አጠቃቀም በ1997 ዓ.ም ሬዲዮ 136፣ ቴሌቪዥን 43 ሰዓታት ተመድቦ ነበር።በ2002ዓ.ም ደግሞ ሬዲዮ 490፣ ቴሌቪዥን 88 ሰዓታት አምድ ደግሞ 776 /ኮለመን/ አምድ ሽፋን ተመድቦ እንደነበር።በ2007 ዓ.ም ደግሞ ሬዲዮ 500 ሰዓታት፣ ቴሌቪዥን 100 ሰዓታትና 700 /ኮለመን/ የአምድ ሽፋን ተመድቦ እንደነበር አስታውሰዋል።