ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዊተርን እንዳይጠቀሙ በዘላቂነት ታገዱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ተጨማሪ የኃይል ድርጊቶችን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ” በሚል ስጋት በዘላቂነት ትዊተር ገጽ እንዳይጠቀሙ ኩባንያው እግድ ጣለባቸው።

ትዊተር ጉዳዩን አስመልክቶ እንዳለው በትራምፕ ላይ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ፕሬዝዳንቱ በአካውንታቸው ላይ “በቅርቡ ያሰፈሯቸውን መልዕክቶች በደንብ ከመረመረ” በኋላ ነው።

አንዳንድ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎችና ታዋቂ ሰዎች ትራምፕ ከትዊተር አስከወዲያኛው እንዲታገዱ ለዓመታት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ሐሙስ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማት ዶናልድ ትራምፕን ከመድረኮቻቸው በማስወገድ “በአደገኛ ባሕሪያቸው” እንዲገፉበት ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጠይቀው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ዋሽንግተን ውስጥ የሚገኘውን ካፒቶል ሒልን የወረሩትን ደጋፊዎቻቸውን “አርበኞች” በማለት ካሞገሱ በኋላ ለ12 ሰዓታት ትዊተርን እንዳይጠቀሙ ታግደው ነበር።

የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት የጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት ለማረጋገጥ ተሰብስበው ባሉበት በመቶዎች የሚቆጠሩት የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ወደ ምክር ቤቱ ግዙፍ ሕንጻ ጥሰው በመግባት በተፈጠረ ግርግር አንድ ፖሊስን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ቢቢሲ አስታውሷል።