ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስደተኞች ጉዳይ አዳዲስ መመሪያዎች አስተላለፉ

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም የትራምፕ አስተዳደር ያሳለፋቸውን ጥብቅ ውሳኔዎችን በመሻር አዲስ የአስተዳደር መመርያዎችን አሳልፈዋል፡፡

ከመመሪያዎቹ መካከል በዋንኛነት የተቀመጠው ልጆችን ከወላጆቻው የነጠለው የስደተኞች ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡

ወላጆችና ልጆች የሆኑ ስደተኞች ተለያይተው የቀሩት በትራምፕ ጊዜ በወጣ የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት ሲሆን፣ አሁን ባይደን ለዚህ ውስብስብ ችግር መፍትሄ የሚሰጥ አንድ አዲስ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ማዘዛቸው ተገልጿል፡፡

ትራምፕ በተለይም በሜክሲኮ ድንበር በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ግዛት ገብተዋል የሚሏቸውን ሰነድ አልባ ስደተኞች ልጆችን ከአዋቂዎች ለይቶ በማስቀረት የወሰዱት እርምጃ ብዙ ውግዘት ያስከተለ ነበር፡፡

አሁን ባይደን ያቋቋሙት አዲስ ግብረ ኃይል እነዚህን ወደ 700 የሚጠጉ ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር ለማገናኘት መንገዶችን ያመቻቻል ተብሏል፡፡

ከአውሮፓዊኑ 2017 እስከ 2018 ብቻ የትራምፕ አስተዳደር 5ሺህ 500 ልጆችን ድንበር ላይ ከወላጆቻቸው ለይቷቸው ነበር፡፡

ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ እንዲያበጅ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የሚመራው የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ሆነው በተሾሙት አለያንድሮ ማዮርካስ አማካኝነት ይሆናል፡፡

በዚህም ልጆች ከተለይዋቸው ወላጆቻቸው በቅርብ ጊዜ እንዲገናኙ መላ ይፈለጋል ተብሏል፡፡

ሌላው ባይደን አስተላለፉ የተባለው አስተዳደራዊ ውሳኔ ትራምፕ ያመጡትን የስደተኞች እና ጥገኝነት አመልካቾችን ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡

ትራምፕ በአሜሪካ ህጋዊ የጥገኝነት ጥያቄዎች የሚስተናገዱበትን መንገድ በመዘጋጋት፣ ሒደቱንም ቀርፋፋ እንዲሆን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡

ከዚህም ሌላ ትራምፕ ለውጭ አገራት የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍን በአመዛኙ መቀነሳቸው ይታወሳል፡፡ ባይደን ይህን የሚቀለብስ ውሳኔንም ፈርመዋል፡፡

ባይደን ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ እንዲህ ብለዋል፣ “አገራችንን ውርደት ማጥ ውስጥ የከተቷትን ያለፈውን (የትራምፕ) መንግሥት የሞራልና የብሔራዊ ሀፍረት ፖሊሲዎች አንድ በአንድ እናጸዳለን፡፡ እናትን ከልጇ መነጠል፤ ያለ አንዳች እቅድ ቤተሰብን መነጣጠል፤ እነዚህ ሁሉ መልክ እንዲይዙ ይደረጋል”

ጆ ባይደን አንድ የሕግ ማእቀፍ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም ዜግነት ለማግኘት ሂደት ላይ ያሉ ሰነድ አልባ የሆኑ 11 ሚሊየን ሰዎችን ሕጋዊ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡