ፖፕ ፍራንሲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለድሃ ሀገራት ጭምር ተደራሽ እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ

መጋቢት 27/2013 (ዋልታ) – የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለድሃ ሀገራት ጭምር ተደራሽ እንዲሆን ለአለም ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፖፕ ፍራንሲስ ይህን ያሉት በቅርቡ የሚከበረውን የትንሳዔ በዓል አስመልክቶ ለህዝበ ክርስቲያኑ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ነው፡፡
ፖፕ ፍራንሲስ ክትባቱን የመግዛት አቅም ለሌላቸው አካላት ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግ ተደራሽ እንዲሆንላቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
በተለይ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ማለታቸውን ዘ ታይምስ መጽሄትን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
84 አመት የሞላቸው ፖፕ ፍራንሲስ ክትባቱን የወሰዱ ሲሆን፣ ቫቲካን ለድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችና ጎዳና ተዳዳሪዎች መከተብ መጀመሯን ተናግረዋል፡፡
ለተጋላጭ የህብረተብ ክፍሎች እና አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢው ትኩረት ካልተሰጠ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ቀላል እንደማይሆን ጠቁመው፣ ለክትባቱ ተደራሽነት ሃብታም ሀገራት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
“በመጨረሻም በተከሰተው ወረርሽኝ ሳቢያ ለሚሰቃዩት ሁሉ ክርስቶስ ተስፋ እና መጽናናትን ይስጥ” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡