18ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር እና 14ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ተጀመረ

የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – በድሬዳዋ ከተማ ከየካቲት 21 እስከ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው 18ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር እና 14ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ተጀምሯል፡፡

ከትግራይ ክልል ውጭ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ በውድድሩ በአጠቃላይ ከ1 ሺህ በላይ የባህል የስፖርት ተወዳዳሪ ልዑክ ታሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ሻኪር አህመድ የባህል ስፖርቶች ወጣቱ ትውልድ የአካባቢውን ትውፊትና ቱባ ባህል እንዲያውቅ እና እንዲያስተዋውቅ ከሚፈጥረው እድል ባሻገር ህዝቦችን በአንድነት እንዲቆሙ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ፌስቲቫሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ መከበሩ፣ የባህል ስፖርቶች ዘርፍ በማጠናከር የህዝቡን ጠቃሚ እሴቶችን ለትውልድ ማስተላለፍ መቻሉ እና ለዘመናዊ ስፖርቶች መሰረት የሚጥል መሆኑ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፣ መጻኢ የሆነውን የነገ እጣ ፈንታ የባህል እሴቶችን ባህል በማድረግ የምንሰራባቸው ባህል ስፖርቶች ለሰላም መረጋገጥና ለሀገራዊ መግባባት ያለውን የማይተካ ሚና የሚረጋገጥበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ሰለሞን አስፋው “ፌስቲቫሉ አብሮነታችንና ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን የምናሳይበት፣ ባህሎቻችንን የምንለዋወጥበት ከመሆኑም ባሻገር ለሀገራዊ መግባባት ያለው ፋይዳ የሚታይበት መድረክ” መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ የባህል ስፖርት ውድድርንና ፌስቲቫሎችን በየደረጃው በማዘጋጀት ለሀገር ገፅታ ግንባታና የብሄር ብሄረሰቦችን አንድነት ለማጠናከር ዋነኛ መሳሪያ ነው ማለታቸውን ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡