በአዳማ ከተማ ለሕዳሴ ግድብ ከ26 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ተበረከተ

በአዳማ ከተማ መስተዳድር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 26 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ መበርከቱን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል እየተዘዋወረ ያለው የሕዳሴ ዋንጫ አዳማ ከተማ ሲደርስ በወታደራዊ ማርሽ የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል በዋንጫ አቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት የከተማዋ ሕዝብ የግድቡ ግንባታ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ 26 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ አበርክቷል።

ዋንጫው አዳማ ከተማ ሲደርስ በከተማዋና አካባቢዋ ሕዝብ ሞቅ ያለ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ከአምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ከንቲባው ገለጻ፣ ገንዘቡ ከባለሀብቶች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ማይክሮ እንተርፕራይዞችና ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች በቦንድ ግዥና በስጦታ የተሰበሰበ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ የፀረ ሰላም ኃይሎች ለሚያደርጉት አፍራሽ የፕሮፖጋንዳ እንቅስቃሴ ትኩረት ሳይሰጥ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ  የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠሉን ገልጸዋል።

በዋንጫው የአቀባባል ሥነስርአቱ ላይ ከተገኙት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የቱለማ አባ ገዳ አቶ አለሙ ባጫ "ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የኦሮሞ ሕዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል በሙሉ አቅማችን እየሰራን ነው" ብለዋል።

ሕብረተሰቡ ለጥፋት ኃይሎች ቦታ ሳይሰጥ ለግድቡ ግንባታ ከዳር መድረስ ከማንኛውም አካል በላይ በባለቤትነት እየተሳተፈ መሆኑን አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሕዳሴ ዋንጫ መዘዋወርን ምክንያት በማድረግ ከጥር 2008 . ጀምሮ ግማሽ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 541 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ገቢ መደረጉን የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ አማን አሊ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በክልሉ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሕብረተሰቡ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል- (ኢዜአ)፡፡