በክልሉ ከመኸር 116 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል

በአማራ ክልል በ2008/2009 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን 116 ሚሊዮን ኩንታል ለመሰብሰብ የተያዘው ዕቅድን ማሳካት የሚቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ ተመለከተ፡፡

በምርት ዘመኑ አራት ነጥብ 46 ሄክታር የእርሻ መሬት በማዘጋጀት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን በቢሮው የሠብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የስራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ሽመላሽ የሻነህ ለዋልታ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ እስከ አሁን ድረስ አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በዘር መሸፈኑን ገልፀው በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚቻል መገምገሙን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ቢሮው በዕቅድ የተያዘውን ምርት ለመሰብሰብ የሰው ኃይሉን በማደራጀት፤ አቅም የማጎልበት ስልጠና በመስጠትና አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን እንዲጠቀም በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ዶክተር ሽመላሽ ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑ የታየው ዝናብና የአየር ሁኔታ እርጥበት አጠር የሆኑ አካባቢዎችን ጨምሮ ከዘር እስከ ፍሬ ድረስ ምቹ መሆኑን አስተባባሪው ይናገራሉ፡፡ በተወሰነ አካባቢ በረዶ ያጋጠመ ቢሆንም ያን ያህል የጎላና ዕቅዱን ሊያዛባ የሚችል አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

‹‹በማሳ ያለው ሰብል ግባችንን ማሳካት የሚችል መሆኑን ያሳያል›› ያሉት አስተባባሪው እንደ ክልል በተካሄደው የአርሶ አደሮች በዓልም ሁሉም ሰብሎች በጥሩ ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመገምገም መቻሉን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ቀድሞ የተዘሩ ምርቶችን በመሰብሰብ እርጥበቱ ሳይለቅ በአንድ ማሳ ላይ በዳግም ምርትና በምርት ቅብብሎሽ ስልት ተጨማሪ ምርት የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡ ይህም በአንድ የምርት ዘመን ሁለት ጊዜ በማምረት ተጨማሪ ምርት ለመሰብሰብ ያስችላል፡፡

በመሆኑም እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚበቅሉና በፍጥነት የሚደርሱ እንደ  ሽምብራ፣ምስር፣ጓያ፣ ማሾን የመሳሰሉ ጥራጥሬዎችና የተለያዩ የገብስ ዓይነቶች እየተዘሩ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚዘንበው ዝናብ ለሰብሎቹ ጥሩ አጋጣሚ መፍጠሩን አስተባባሪው ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ስልት 364ሺ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ እስከ አሁን 250ሺ ሄክታር ያህሉ በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ሰብሉ ደርሶ መድረቅ ብቻ በሚጠብቅ 36ሺ 430 ሄክታር መሬት ከላይ የተጠቀሱትን ሰብሎች ለመዝራት ላይ ታቅዶ 51 ሺ ሄክታር መሬቱን በዘር ለመሸፈን ተችሏል፡፡

እስከ አሁን ድረስም 937ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ተሰብስቧል፡፡ ይህም እንደ ክልል ከተዘራው 21  በመቶውን ይሸፍናል፡፡