ከዘንድሮ የመኸር ወቅት 320 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይጠበቃል

በዘንድሮ የመኸር ወቅት በአጠቃላይ 320 ሚሊዮን ያህል የሰብል ምርት ይሰበሳባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሮክቶሪየት ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰመድ አብዲ ለዋልታ እንደገለጹት በ2008/09 የምርት ዘመን በአጠቃላይ ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ  በሰብል የተሸፈነ ሲሆን  320 ሚሊዮን  ኩንታል የሰብል ምርት እንደሚሰበሰብ ተገምቷል ።

በዘንድሮ የመኸር ወቅት አምና በኢል ኒኖ ምክንያት የተከሰተውን የምርት ጉድለት ለማካካስ እንዲሁም  ምርትና ምርታማነተን ለማሳደግ  በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለአርሶ አደሩ የተለያዩ  ድጋፎች ሲደረጉ መቆየቱን አቶ አብዱልሰመድ ተናግረዋል ።

በመኸር ወቅት በአገሪቱ አብዛኛዎቹ ክፍሎች ለግብርና ተስማሚ የሆነ የዝናብ ሥርጭት እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብዱልሰመድ በመኸር ወቅት የነበሩት ቅድመ ዝግጅቶችና ለአርሶ አደሩ የተሠጡት ተግባር ተኮር ሥልጠናዎች እንዲሁም የተደረገው ክትትል የታቀደውን ምርት ለማገኘት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ አብዱልሰመድ አስረድተዋል ።

በተጨማሪም በመኸር ወቅት በአገሪቱ ለሚገኙ አርሶአደሮች 9ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ከ 275ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መቅረቡንና የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ለማግኘት የታቀደውን ምርት ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው አቶ አብዱል ሰመድ አክለው ገልጸዋል ።

እንደ አቶ አብዱል ሰመድ ገለጻ የሰብል ምርት ላይ ጉዳት የሚያደርሱትን ተባዮችንና የዋግ በሽታን በቅድሚያ ለመከላከል 264ሺ 599 ሊትር የፀረ ዋግ ኬሚካልን በመኸር ወቅት በማሠራጨት የበሽታ መከላከል እርምጃዎችን ለማጠናከር ተችሏል።

በተለይ በአገሪቱ ቆላማና የወይና አደጋ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የደረሱ ሰብሎች በብዛት እየተሰበሰቡ መሆኑን  የሚገልጹት አቶ አብዱልሰመድ  የደረሰ ሰብል በድንገተኛ ዝናብ እንዳይበላሽ በማሰብ ከብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባባር ለአርሶአደሩ  መረጃዎች  በፍጥነት እንዲደርሰው እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ። 

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ  የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ  ጥንቃቄ በማድረግ  ህብረተሰቡን ያሳተፈ የሰብል መሰብሰብ ሥራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግና  ድንገተኛ ዝናቡን ለቀጣይ የመስኖ ሥራ  ማዋል እንደሚገባ አቶ አብዱል ሰመድ አሳስበዋል ።  

በ2007/08 የመኸር ወቅት 263ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መገኘቱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።