ክልሉ የሰብል ብክነትን ወደ 10በመቶ ለማውረድ እየሰራ መሆኑ ገለጸ

በአርሶ አደሩ የሚሰበሰበው ሰብል ብክነት እስከ 10 በመቶ ለማውረድ እየተረባረቡ መሆናቸውን የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማሜ ገሩማ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤በክልሉ በየዓመቱ ከሚሰበሰበው ሰብል ከ15 እስከ 25 በመቶ እየባከነ እንደነበር ጠቁመው ፤ ዘንድሮ ግን ብክነቱን ከ5 እስከ 10 በመቶ ለመቀነስ በመረባረብ ላይ ናቸው ፡፡

በክልሉ በተለይም ጤፍ ሲታጨድና በሰው ትክሻ ሲጓጓዝ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚራገፍ ነው ያመለከቱት ፡፡

በተጨማሪም ሰብሉ በሚከመርበት ፣በሚወቃትና በሚጓጓዝበት ወቅት ብክነቱ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ይኽንን ችግር ለማቃለል በተለይም በሸሎቆውና በቆላማ አከባቢዎች ላይ አርሶ አደሩ ባብዛኛው በማሽነሪዎች ሌላውም በከፍተኛ ጥንቃቄ ምርቱን እየሰበሰበ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

ዘንድሮ በዋና ዋና ሰብሎችን 1ነጥብ 1ሚሊየን ሄክታር ላይ በአዝርዕት ፣በስራስር፣ በጥራጥሬና የብርዕ ሰብሎች ከተሸፈነው መሬት 66 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ፡፡

በክልሉ እስካሁን በሰው ኃይልና በማሽነሪዎች እየተደረገ ባለው ርብርቦሽ በቆላማ፣ በወይናደጋማ እና በደጋማ አከባቢዎች ከደረሱ ሰብሎች 62 በመቶ መሰብሰቡን አስታውቀዋል ፡፡

ዓምና በድርቅ ምክንያት በተወሰኑ የክልሉ አከባቢዎች ላይ በተወሰነ ደረጃ የሰብል ጉዳት ነበር ያሉት አቶ ግርማሜ ፡፡

የዓምናው ምርት ካሁኑ ጋ ሲነጻር ከ35 አስከ 40 በመቶ ጭማሪ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል  ፡፡

የዚሁ ምክንያትም ዘንድሮ የተስተካከለ ዝናብ ስለነበር፣ የጎላ ሰብል በሽታም ባለመኖሩና ፣አርሶ አዴሩም ከዓምናው ድርቅ ትምህርት በመውሰድ በበቂ ግብኣትና በበቂ ዝግጅት ስራው በማከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁንም አርሶ አደሩ የሰብል ብክነት መከላከክል ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ  የደረሱት ሰብሎች በፍጥነት እንዲያነሳ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል ፡፡