በደረቅ ወደቡ አገልግሎት የጀመረው ማሽን የፍተሻ ጊዜን አሳጥሯል

በሞጆ ደረቅ ወደብ   አገልግሎት   መሥጠት  የጀመረው  አዲስ የፍተሻ  ማሽን ኮንቴነሮችን ለመፈተሽ የሚጠፋውን ጊዜ  ማሳጠሩ ተገለጸ ።   

ባለፈው  ሳምንት   አገልግሎት  መሥጠት የጀመረውን ዘመናዊ   የጉምሩክ  የፍታሻ  ማሽን የተከለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን  ነው ።   

የሞጆ ደረቅ ወደብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ወርቁ ለዋልታ እንደገለጹት ቀደም ሲል ወደ  ወደቡ  የሚገቡና የሚወጡ የጭነት ኮንቴነሮች የሚፈተሹት ከእያንዳንዱ ኮንቴይነር  ናሙና  በመውሰድ በመሆኑ  የፍተሻ አገልግሎቱን  ረጅም ጊዜ  የሚወስድ  አድርጎታል ። 

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በኢትዮያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተተከለው አዲሱ  ዘመናዊ የፍተሻ ማሽን ባለፈው ሳምንት ሥራ ከጀመረ አንስቶ ግን ከእያንዳንዱ ኮንቴይነር  ናሙና  በመውሰድ   በፍተሻ ሥራው የሚባክነውን  ጊዜ  ለመቆጠብ አስችሏል ። 

ዘመናዊ ማሽኑ ከጭነት ኮንቴይነሮች ናሙና  መውሰድ ሳያስፈልግ በአንድ ጊዜ  ብዛት ያላቸውን ኮንቴይነሮችን ለመፈተሽ የሚያስችል ነው ብሏል ።

የጭነት ኮንቴይነር  ባለቤቶች የደረቅ ወደብ  መጋዘን  ኪራይ ሳይበዛባቸው  ሰነዶቻቸውን በማቅረብ ብቻ በአፋጣኝ  ኮንቴይነራቸውን  ለማንሳት  ምቹ   ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል ።

ባለፈው  የበጀት ዓመት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ባወጣው የአሠራር መመሪያ መሠረት የትኛውም  ድርጅት  ከስድስት ወር በላይ  እቃዎችን የያዙ  የጭነት  ኮንቴይነሮች  በደረቅ  ወደቦች ላይ እንዲቀመጥ ካደረገ  የሚወረስበት መሆኑን ነው ያነሱት፡፡   

ስለሆነም በዘመናዊ  የፍተሻ ማሽን  የታገዘ  አገልግሎት መጀመሩ  የኮንተይነር ባለቤቶች ኮንቴይነሮቻቸው  እንዳይወረሱ  እገዛ እንደሚኖረው  ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል ።    

የሞጆ ደረቅ ወደብ  በአጠቃላይ 14ሺ  የሚሆኑ   የጭነት ኮንቴይነሮችን   የመያዝ አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል  ።