በአዲስ አበባ ከተማ በ3 ቢሊየን ብር በጀት ከ206 ሺህ በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ 206 ሺ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሠማራት ታቅዶ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ናቸው ።
ከነዚሁም ውስጥ 103 ሺህ ወጣቶች በህብረተሰብ አቀፍ የአካባቢ ልማት ሥራዎች እንደሚሠማሩ ጠቁመዋል፡፡
ቀሪ ወጣቶቹም በአረንጓዴ ልማትና በመንገድ ሥራዎች ላይ በስፋት ለማሠማራት መታቀዱን ነው ያስታወቁት ።
ለሥራ ዕድል ፈጠራ ማስፈጻሚያም 3 ቢሊየን ብር በጀት መመደቡን ሃላፊው አስታውቀዋል ፡፡
የከተማው አስተዳደር ባካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ መሠረት የወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መሪ ዕቅድ ወጥቶ ለተለያዩ ሴክተር ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች ምን ያህል የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባቸው መቀመጡን አቶ ልዑልሰገድ አብራርተዋል ።
ለዚህም በመዲናዋ የሥራ አጡን ቁጥር ለመለየት ቤት ለቤት ምዝገባና የማጥራት ሥራ 80 ሺ189 ያህል አዲስ ሥራ ፈላጊ ወጣት መኖሩ መረጋጋጡን አስታውቀዋል ።
አስተዳደሩ ያወጣውን መሪ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ 68ሺህ 700 የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች ማወያያት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም “ሥራ አጥ ወጣቶች ሊሰማሩባቸው የሚፈልጓቸውን የሥራ መስክ እንዲመርጡ በማድረግ ሥልጠናዎች እየተመቻቹ ይገኛሉ፤” ብለዋል ።
እስካሁን ድረስም በመጀመሪያ ዙር 24ሺ 400 የሚሆኑ ወጣቶች በማኑፋክቸሪንግ ፣ በኮንስትራክሽን ፣በንግድ፣ በአገልገሎትና በከተማ ግብና ሙያዎች ሥልጠናዎችን መውሰድ እንደጀመሩ መግለጻቸውን የዘገበው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነው ።