ባለስልጣኑ ከመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሾች በመንገድ ግንባታ ስራ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖብኛል አለ

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሾች በመንገድ ግንባታ ስራ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖብኛል አለ

ከገርጂ ሮባ ዳቦ – መብራት ኃይል ያለውን ነባር መንገድ ደረጃ የማሳደግ ግንባታ ስራ ቢጀመርም ከመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሾች በግንባታ ስራው ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ሆነዋል ተባለ፡፡

ከመኖሪያ ቤቶቹ የተገናኙት እነዚህ የፍሳሽ መስመሮች የግንባታው የቁፋሮ ስራ በሚከናወንበት ወቅት ከዝናብ ውሃ መፋሰሻ (ድሬኔጅ) መስመሮች በመውጣት በአካባቢው ላይ ከፍተኛ መጥለቅለቅ በመፍጠርና በቁፋሮ ስራው ላይ የመስመሮቹ ፍሳሽ ባለመቆሙ ምክንያት የግንባታ ስራውን በተገቢውም መንገድ ለማስኬድ እንቅፋት ሆኗል፡፡

ይህንን ችግር በዚህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ እንቅፋት በመፍጠሩ ከመኖሪያ ቤቶች ወደ መንገድ የወጡና በግንባታው ምክንያት የፍሳሾ መስመር የተቆረጡ መስመሮችን በመዝጋት ተገቢውን ማስተካከያ ህብረተሰቡና የሚመለከተው አካላት እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ስራ አጠቃላይ 945 ሜትር ርዝመትና 2ዐ ሜትር ስፋት እግረኛ መንገድን ጨምሮ በማከናወን ላይ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡