በተለያየ ምክንያት ግንባታዎችን የሚያጓትቱ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎችን የከተማ አስተዳደሩ አይታገስም – ኢ/ር ታከለ ኡማ

በተለያየ ምክንያት ግንባታዎችን የሚያጓትቱ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎችን የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር  ታከለ ኡማ አሳሰቡ፡፡

ምክትል ከንቲባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ላይ ለሚሳተፉ የህንፃ ተቋራጭ ባለቤቶች እና አማካሪዎች የስራ መመርያ ሰጥተው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለብክነት የተጋለጠ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በግንባታ ላይ ያሉ ነባር ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸዉ ጊዜ ውስጥ የማይጠናቀቁ ከሆነ ውላቸው እንደሚቋረጥ ያሳወቁት ኢንጅነር ታከለ ኡማ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የተሰጧቸውን ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ያልቻሉ እና የህዝብን ሃብት ለከፍተኛ ብክነት እየዳረጉ ያሉ ኮንትራክተሮች እና አማካሪዎች በቀጣይነት የከተማ አስተዳደሩ በሚያሰራው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት ግንባታዎችን የሚያጓትቱ ኮንትራክተሮች እና አማካሪዎችን የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ሁሉም በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡት ግንባታዎች በአስቸኳይ ኦዲት ተደርገው ለከተማ አስተዳደሩ ኮንስትራክሽን ቢሮ ሪፖርት እንዲያደርጉ እና ኮንትራክተሮች እና አማካሪዎች ፕሮጀክቶችን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ አጠናቅቀው እንዲያስረክቡ አሳስበዋል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)