የሽሮ ሜዳ-ቁስቋም እና የአቃቂ-ቱሉዲምቱ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ

የሽሮ ሜዳ-ቁስቋም እና የአቃቂ-ቱሉዲምቱ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን በመዲናዋ አዳዲስ መንገዶችን በመገንባትና በአገልግሎት ብዛትና በሌሎች ምክንያቶች የተበላሹትንም በመጠገን ከተማዋ የተሻለ የመንገድ መረብ እና የትራፊክ ፍሰት እንዲኖራት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በትላንትናው እለትም የዚሁ አካል የሆነው 1.4 ኪሎሜትር ርዝመትና 30 ሜትር የጎን ስፋት ያለው የሽሮሜዳ – ቁስቋም አስፓልት መንገድ እና ከ5 ኪሎሜትር በላይ ርዝመትና 25 ሜትር የጎን ስፋት ያለው የአቃቂ-ቱሉ ዲምቱ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶችን አስጀምሯል፡፡

ፕሮጀክቶቹን መርቀው ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ የተጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ እና ግንባታቸው ሲጠናቀቅም ከሚኖራቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር የከተማዋን ገፅታ ያሻሽላሉ ብለዋል፡፡

ሁለት ዓመት ከሚፈጁት ከነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ ከ120 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በራስ ኃይል እና በተቋራጮች አማካኝነት በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)