በ1ነጥብ14 ቢሊዮን ብር በጊደቦ ወንዝ ላይ የተገነባው የግድብ ሊመረቅ ነው

በ1ነጥብ14 ቢሊዮን ብር በጊደቦ ወንዝ ላይ የተገነባው እና 13,425 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት የሚያስችለው ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሊመረቅ እንደሆነ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ከ10 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችንና ከ192‚000 በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የእርሻ ኢንቨስትመንትንም በአካባቢው ይስባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የግድቡ ውሃ የመያዝ አቅም 62ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ግንባታው 25ነጥብ 8 ሜትር ከፍታ እና 335 ሜትር ርዝመት አለው፡፡

የጊዳቦ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ከዲላ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ 17 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ ደግሞ 376 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሚገኝ ሲሆን ሥራው የተጀመረው የካቲት 2002 ዓ/ም ነው ፡፡

ግድቡ እስከ 4ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ውሃ እንዲተኛ ስለሚያደርግ 1200 ሄክታር ስፋት ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ይፈጥራልም ተብሏል፡፡

በፕሮጀክቱ ግንባታ ወቅት የዲዛይን ለውጥ መደረጉና ዲዛይኑ በወቅቱ ተሠርቶ ባለመቅረቡ የግድቡ ግንባታ ይጠናቀቃል በተባለበት ጊዜ አለመጠናቀቁንም ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል ፡፡  

የጊዳቦ ግድብ ጥር 14/2011 ዓ.ም የሬዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችና የፕሮጀክቱ ሥራ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት ይመረቃል፡፡