የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ድርጅታዊ ግምገማ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላለፈ

ጋምቤላ፤ ጥር 02 2004 /ዋኢማ/ – የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋህአዴን/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ድርጅታዊ ግምገማ ራሱን በጥልቀት በመፈተሽና በማጥራት ክልሉን ወደ ተሻለ ልማት ለማምራት የሚያስችለውን ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

የጋህአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የክልሉ መንግስት ተጠሪ አቶ አኩኝ ቡያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከታህሳስ 18 እስከ 30/2004 ዓመተ ምህረት ባካሄዱት ግምገማ ያለፉትን አምስት ወራት የልማት፣የመልካም አስተዳደርና የድርጅት ስራዎችን አፈፃፀም ተመልክተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በግብርና ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች ላይ የአፈጻጸም ውስንነትና ሥራዎቹ በሚፈለገው ደረጃ አለመንቀሳቀሳቸውን ማዕከላዊ ኮሚቴው በግምገማ ማረጋገጡን አቶ አኩኝ ገልጸው፤ይህም የክልሉን አመታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አተገባበር ከሚገመተው በላይ አዝጋሚ እድርጎታል ብለዋል፡፡

የአመራር አካላቱ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውንና ቡድንተኝነት በማራመድ በተለይም የህዝቡን ድህነትና ኋላቀርነት በማሻሻል ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚኖረዉን ህዝቡን በመንደር የማሰባሰብ ስራ ዘንግተውት ባለፉት አምስት ወራት ሥራው ሳይካሄድ መቅረቱን አመልክተዋል ፡፡

በተለይም በክልሉ ከፍተኛ አመራር ዘንድ እየሰፋ የመጣው የቡድንተኛነትና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የአመራሩን ወደተግባር የመግባትና ድርጅታዊ ተልዕኮን በግንባር ቀደምነት የመፈጸም አቅም እተፈታተነው መምጣቱን ማዕከላዊ ኮሚቴው በግምገማው መገንዘቡን ኃላፊው አስታውቀው፤ ሁኔታውን መለውጥና ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል ፡፡

በዚህ መሰረት የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጓነር የር ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን ፣ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚዎች አቶ ኮር ፖችና ጀምስ ዴንግ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ድርጅቱ ባካሄደው ግምገማ መወሰኑን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ኡሞድ ኡቦንግ ደግሞ የድርጅቱንና የመንግስት ስራ ደርበው ለመስራት ድርጅቱ ያወጣው አዲስ መመሪያ ስለማይፈቀድ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ መደረጉን አቶ አኩኝ ገልጸው፤የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩትን አቶ ጋትልዋክ ቱት የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ በመሾም ሙሉ ጊዜያቸውን በድርጅቱ ስራ እንዲያውሉ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴነት ዝቅ ባሉት ምትክ አቶ ሙሉጌታ ሩት እና አቶ ፒተር ጋርኮት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

የድርጅቱ ግምገማና የማጥራት ስራ በየደረጃው በከተማ መስተዳደሮች፣ ማዘጋጃ ቤቶች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና በቀበሌ መስተዳደሮች አባላት ላይ ከጥር ሁለት ጀምሮ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ተመሳሳይ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡

የአመራር አባላቱ ከቡድንተኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ዝቅጠት ወጥተው በአዲስ መንፈስ በአንድ አመለካከት ለፈጣን ልማትና ለመልካም አስተዳደር በሚደረገው ርብርቦሽ ህዝቡ ከጎናቸው ሆኖ እንዲታገል አቶ አኩኝ ቡያ ጥሪ አስተላልፈዋል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡