አዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ የአፍሪካና የቻይና ወዳጅነትን እንደሚያሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለፁ

አዲስ አበባ፤ጥር 03 2004 /ዋኢማ/ – አዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ የአፍሪካና የቻይና ወዳጅነት በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለጹ።

ለአዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ ግንባታና ለውስጥ ቁሳቁስ ማሟያ 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንባታው የተጠናቀቀውን አዲሱን የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ ትናንት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት የሕንጻው መገንባት አፍሪካና ቻይና ወደፊት በትብብር ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት የሚያመላክት ነው።

በሕንጻው ግንባታ ላይ ኢትዮጵያ 130 ሺህ ስኩዌር ሜትር መሬት በነፃ በመስጠትና የግንባታ ዕቃዎቹ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ከማድረግ በተጨማሪ የቻይና መንግስት ሕንጻውን እንዲገነባ ከአፍሪካ ኀብረት ጋር በመሆን የማግባባት ሥራ መስራቷን ጠቁመዋል።

ሕንጻው የአፍሪካ ኀብረትን የቢሮና የስብሰባ አዳራሽ ፍላጎት እንዲያሟላ ተደርጎ የተገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልጸዋል።

ለአዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ ግንባታና ለውስጥ ቁሳቁስ ማሟያ 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን አጠቃላይ ወጪው በቻይና መንግስት የተሸፈነ ነው።

በሕንጻው ውስጥ ያለው ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ በአንድ ጊዜ ከ2 ሺህ 5 መቶ በላይ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ሲኖረው ስድስት መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾቹ እያንዳንዳቸው 700 ሰዎችን ሲይዙ አራት አዳራሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው 115 ሰዎችን የሚይዙ ናቸው።

በተጨማሪም ሕንጻው ያሉት 31 ትናንሽ አዳራሾች እያንዳንዳቸው እስከ 30 ሰዎች የሚይዙ ሲሆኑ አራት የመሪዎች ማረፊያና መወያያ አዳራሾች እንዲኖሩት ተደርጎ ተሠርቷል።

የአፍሪካ አገራት ባህላዊ ትርዒት የሚያሳዩበት እስከ አንድ ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው አንፊ ቲያትር እና መለስተኛ አውሮፕላን ወይም ሄሊኮፕተር የሚያርፍበት ቦታ በግቢው ውስጥ ተገንብቷል።

በከፍተኛ ወጪ የተገነባው አዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ በያዝነው የጥር ወር አጋማሽ ላይ በሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ በይፋ ይመረቃል።

የሕንጻውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረጉት ጉብኝት የአፍሪካ ኀብረት ሊቀ መንበር ዶክተር ጃን ፒንግ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፍሰሀና የኀብረቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሕንጻ ግንባታ የተጀመረው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጣር ጥር 2009 ሲሆን ከሦስት ዓመት በኋላ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።