መንግሥት የመምህራን፣ የርዕሳነ መምህራንና የሱፐር ቫይዘሮችን የደሞዝ ስኬል አሻሻለ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4 /2004 (ዋኢማ) – የመንግሥት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን የርዕሳነ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የደሞዝ ስኬል ማሻሻያ ማድረጉን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለመምህራን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ይሰጣል ብሏል፡፡

የሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታዎች ዛሬ በጋራ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የደሞዝ ማሻሻያው በኢትዮጵያ መምህራን በተመለከተ የተካሄደውን ጥናት መሠረት ያደረገ ነው ፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን እንዳብራሩት የመምህራን የደሞዝ ስኬልና የሙያ ደረጃ ማሻሻያ ጥናት ባለፈው ሳምንት ለመንግሥት ቀርቦ ጸድቋል፡፡

አዲሱ የደሞዝ ማሻሻያ ከመጋቢት 1ቀን 2004 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው፣ የሙያ ብቃት ደረጃን መሠረት ያደረገው ማሻሻያው ታሳቢ ያደረገው በአገሪቱ ያለውን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሁነኛ መሣሪያ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ማሻሻያው የትምህርት ጥራትን ከመምህራን ብቃት ማዳበር ጋር የተያያዘ መሆኑንና መምህራን ብቃታቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረትና በተማሪዎቻቸው ላይ በሚያመጡት ውጤት የአገር እድገትንና ልማትን ለማፋጠን ተብሎ መፈቀዱን አስረድተዋል።

መንግሥት ለሙያው የተለየ ትኩረት በመስጠት ከሲቪል ሰርቪሱ የተለየ የደሞዝና የዕድገት እርከን ማሻሻያ ለዘርፉ መስጠቱን ዶክተር ምሥራቅ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ባለፈው ዓመት ለመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ማሻሻያ ሲያደርግ ለመምህራንም ጭማሪ ማድረጉን አስታውሰው፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን የትምህርት ደረጃ ከሰርተፊኬት ወደ ዲፕሎማ ከፍ በማለቱ ለሙያው ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች የተለየ የመነሻ ደሞዝ ሰኬል እንደወጣ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ እርከን በስድስት ሲቆም፣ የመምህራን ግን ሰባት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት አንድ የዲፕሎማ ምሩቅ ጀማሪ መምህር የመነሻ ደሞዝ 1ሺህ 114 ብር ሲሆን፣ማስተማር ሲጀምር ወደ 1ሺህ172ብር ከፍ ይላል። የመነሻ ደሞዙ ወደጎን በእርከን እያደገ መጥቶ ጣሪያው 1ሺህ 719 ብር እንደሚደርስ ተናግረዋል፡፡

ጀማሪው መምህር ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ ከዚያም ወደ ሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ብቃትና ዝግጅቱን በየደረጃው የማሻሻል ዕድሉ የተመቻቸ መሆኑን ዶክተር ምሥራቅ አስረድተው፣በዚህም ዕድሉ ተጠቅሞ የራሱን ብቃት በየደረጃው ሲያሻሽልና በሥራውም ውጤት ሲያስመዘግብ ደሞዙ እንደሚጨምር አስታውቀዋል፡፡

መምህሩ በየደረጃው በሚሰጠው የሙያ ፈቃድ የደሞዝ ስኬሉ እንደሚያድግና ርዕሰ መምህር ወይም ሱፐር ቫይዘር ሲሆን፣ ለጀማሪ ርዕሰ መምህር መነሻው 5ሺህ 554 ብር እንደሚሆንና ይህም ከሙያ ልምዱ ጋርና ነባሩ ደረጃ ታይቶ ዘጠኝ እርከን ያለው የደሞዝ ዕድገት ጣሪያ መመደቡን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም አስረድተዋል፡፡

በዕድገት መሰላል መሪ ርዕሰ መምህርና ሱፐርቫይዘር የሚሆኑ መምህር የመጨረሻ የደሞዝ ጣሪያ 7ሺህ 768ብር መሆኑን ገልጸው፣ በጀማሪ መምህርና በርዕሰ መምህር መካከል ቀድሞ የነበረው ባለ12 ደረጃ የዕድገት መሰላል አሁን በሁለት ደረጃ አድጎ 14 መድረሱን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በመምህራን ለቀረበውው የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ለመምህርነት ሙያ የተለየ ክብር ማጎናጸፉን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

የመምህራን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ በሙከራ ደረጃ ዘንድሮ መስጠት እንደሚጀመርና ፈቃዱ በየሦስት ዓመቱ እንደሚታደስ አስረድተዋል፡፡

አንድ መምህር ከአንድ ደረጃ ወደሌላው ለመሸጋግር የምዘና ሥርዓት እንደተቀመጠለት አመልክተው፣ የሙያ ፈቃድ ማውጣቱ፣ ተከታታይነት ያለው የሙያ ማሻሻያ መውሰዱና በተማሪዎቹ ላይ ተጨባጭነት ያለው ለውጥ ማምጣቱ ማሟላት የሚገባው የሙያ መስፈርት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ይህም መምህሩን ዕድገቴን ጨርሻለሁ ብሎ እንዳይቀመጥና በየዓመቱ ለ60 ሰዓት ተከታታይ ስልጠና እንዲወስድና ሙያውን እንዲያሻሽል ያተጋዋል ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ በሙያው ላይ ለረዥም ዓመታት እንዲቆይ፣በሚያመጣው ውጤት በኅብረተሰቡ ዘንድ የተከበረ ሙያ ባለቤት ተደርጎ እንዲቆጠርለት ያበረታታዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለሕክምናና ለመምህርነት ሙያዎች በሰጠው የተለየ ትኩረት በቅድሚያ በነዚህ የሙያ ዘርፎች የሚሰማሩ ዜጎችን ከወጪ መጋራት ነጻ በማድረግ ያበረታታል ሲሉም ተናግረዋል።
በክረምትና በበጋ ወቅቶች ጭምር መምህራን በመንግሥት ወጪ እንዲሰለጥኑ ማድረጉ ለሙያው ትኩረት መስጠቱን እንደሚያመለክትም አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት 85ሺህ መምህራን ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ ደረጃቸውን ለማሻሻል ትምህርት እየተከታተሉ ናቸው። 56ሺህ መምህራን ከመጀመሪያ ዲግሪ ወደ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም 20ሺህ ርዕሳነ መምህራን ወደተሻለ የትምህርት ደረጃ ራሳቸውን በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

shares