በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ያተኮረና “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተሰኘ መፅሐፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/ዋኢማ/ – የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር በአቶ በረከት ስምኦን የተጻፈ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ በሸራተን አዲስ ተመረቀ።

መፅሐፉ አሥር ምዕራፎችና 314 ገፆች ሲኖሩት በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄዱት በምርጫ 97 እና 2002 እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን በምረቃው ወቅት ተጠቅሷል። 

በምረቃው ሥነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፤ የመፅሐፉ መመረቅ በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት የተደረጉ ውጣ ውረዶችን ለተተኪው ትውልድ ለማስተማር ያገለግላል።

በተጨማሪም የመጽሐፉ ለእንባብያን መድረስ ሀገሪቱ ለተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ ስኬትና ለዲሞክራሲ መጎልበት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ ደመቀ  አስረድተዋል።

የመጽሐፉ ደራሲና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው፤ መጽሐፉ ፖለቲካዊ ይዘት ቢኖረውም በውስጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርጫ 97 ወቅትም ሆነ በምርጫ 2002 ያልተጠበቁ ውጤቶች መገኘታቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ ለውጤቱ መገኘት ምክንያቶቹን በመጽሀፋቸው ውስጥ ማካተታቸውን አስረድተዋል።

ይህን መጻሐፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ምክንያትን ሲገልጹም በሁለቱም ምርጫዎች ወቅት ለህዝብ ገልጽ ያልሆኑና በሳቸው ብቻ በሚስጥር ተይዘው የነበሩ ጉዳዮችን ለህዝብ ለማሳወቅ አስበው እንደሆነም አስረድተዋል።

በመፅሀፉ ውስጥም ማሟሻ ወግ፣ ድምጽ መስጠት፣ ቆጠራና ያልተገመተ የምርጫ ውጤት፣ “ሁሉን ታገኛለህ ወይም ሁሉን ታጣለህ”፣ እንደገና ሌላ ቅድመ ምርጫ፣ የዜሮ ድምር ፖለቲካ በተግባር፣ ምርጫ 2000 ትንሿ አስደንጋጭ ምልክት የሚሉና ሌሎች ታሪኮች በመጽሐፋቸው ውስጥ መካተታቸውን ተናግረዋል። 

ለመፅሐፉ ማሳተሚያ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ሲሆኑ፤ የመጽሐፋ መታተም ለአሁኑ ትውልድ ጥንካሬንና ጽናትን ለማስተማር ይረዳል በማለት በመፅሀፉ ምረቃ ወቅት ተናግረዋል።

በመፅሀፉ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ አርቲስቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።