ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 124 የሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2004/ዋኢማ/ – ባለፉት አምስት ወራት ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶች 124 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ተገልጿል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ 123 ነጥብ 98 ሚሊየን ዶላር ገቢው የተገኘው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግና የፋርማሲቲካልና ከኬሚካል ምርት ውጤቶችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ ነው።

ከተገኘው ገቢ 62 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ 38 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ 19 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ከአግሮ ፕሮሰሲንግና 3 ነጥብ 08 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ከፋርማሲቲካልና ከኬሚካል ውጤቶች የተገኘ  መሆኑን ተገልጿል።

እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለፃ ባለፉት አምስት ወራት 161 ነጥብ 11 ሚሊየን ዶላር ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ የእቅዱን 76 ነጥብ 95 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

እቅዱን መቶ በመቶ ማድረስ ያልተቻለው ሰፊ እቅድ በመታቀዱና በውጭ ያሉ ሀገራት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል።

ሆኖም ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከተገኘው 63 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶችን ለማሳደግ በያዘው እቅድ መሰረት ዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን አቶ መላኩ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።