በብሪታኒያ የሚኖሩ ከ350 በላይ ኢትዮጵያውያን በዲያስፖራ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ, ታህሳስ 14 ቀን 2004 (ዋኢማ) – በብሪታኒያ የሚኖሩ ከ350 በላይ ኢትዮጵያውያን በዲያስፖራ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ በውይይቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ነጋ ጸጋዬ በአገር ግንባታ ረገድ ዋነኛው ሃይል የሆነውን የህዝብ ተሳትፎ ማጎልበት የመንግስት ልዩ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

 

መንግስት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ጋር ያላቸው ትስስር ይበልጥ ጎልብቶ በልማት ዙሪያ ሚናቸው ከፍ እንዲል በርካታ አዋጆችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን እንዳወጣ ጠቅሰዋል።

የህግ ማእቀፎቹ የዜጎችን ጥቅሞችና መብቶች በማስከበር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በውጭ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያን በአሁኑ ወቅት ንብረት የማፍራት፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና ንግድ እንቅስቃሴዎች እንደሌሎች ወገኖቻቸው የመሳተፍና ሌሎች መብቶቻቸውም በህግ እንደተረጋገጡላቸው ጠቁመዋል።

በህዳሰው ግድብ ግንባታ ዲያስፖራው የሚያደርግው ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዳለውና ቦንዱን በመግዛት የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ከልሌ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰጡት ማብራሪያ መንግስት በውጭ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ለማሳደግ ደህንነትና መብቶቻቸውን መጠበቅ፣ የኮሙኒቲ አባላትን መርዳት፣ ዜጎች በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያላቸውን ተሳትፎ ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በብሪታኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ በበኩላቸው ረቂቅ ፖሊሲው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብቶችና ጥቅሞችን በማስከበር የወደፊት ተሳትፏቸውን የሚያጠናክር ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያኑ ከውይይት በኋላ ለታላቁ የህዳ ግድብ 235 ሺህ ብር የሚያወጣ ቦንድ መግዛታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዕህፈት ቤት መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።